ሪጅኑ በማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የሚስተዋለውን የኃይል ጭነት መጨናነቅ ለመቅረፍ እየሰራ ነው

ሪጅኑ በማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የሚስተዋለውን የኃይል ጭነት መጨናነቅ ለመቅረፍ እየሰራ ነው

በኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሚስተዋለውን የኤሌክትሪክ ጭነት መጨናነቅ ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማዕከላዊ 3 ሪጅን መምሪያ አስታወቀ።

‎የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ እስማኤል ሙዘይን እንደገለፁት ሪጅኑ ከሚያስተዳድራቸው 20 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች መካከል አስራ አንዱ የሚገኙት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው።

‎የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎቹም ሆኑ የማስተላለፊያ መስመሮቹ ከፍተኛ የሆነ የኃይል ጭነት የሚበዛባቸው በመሆኑ ለተደጋጋሚ የኃይል መቋረጥ እንደሚጋለጡ ተናግረዋል።

‎እንደ አቶ እስማኤል ገለፃ የኤሌክትሪክ ኃይል ጭነት መጨናነቅ እየተከሰተ ያለው በማከፋፈያ ጣቢያዎቹ ላይ ያለው የኃይል ፍላጎት ከትራንስፎርመሮቹ አቅም በላይ በመሆኑ ምክንያት ነው።

‎በአሁኑ ወቅት በማከፋፈያ ጣቢያዎቹ እና ማስተላለፊያ መስመሮቹ የሚስተዋለውን ከፍተኛ የሆነ የኃይል ጭነት መጨናነቅ ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ፕሮጀክት ተቀርፆ ወደ ሥራ መገባቱንም ነው የጠቆሙት።



‎በዚህም በአዲስ ሴንተር፣ ጎፋ እና መካኒሳ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የትራንስፎርመር እና የማስተላለፊያ መስመር አቅም የማሳደግ ሥራዎችን ለማከናወን መታቀዱን ገልፀዋል።

‎በአፍሪካ ህብረት አካባቢ አዲስ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ለመገንባት መታቀዱን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ጣቢያው አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የኤሌክትሪክ አቅርቦት አስተማማኝነትን ለማሳደግ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።

‎በአንፎ ሜዳ እና ቃሊቲ 2 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙትን ባለ 25 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሮችን ወደ 50 ሜጋ ቮልት አምፒር የማሳደግ ሥራ ለመስራት መታቀዱንም ተናግረዋል።

‎በሰበታ 1፣ አዲስ ዌስት እና ጥቁር አንበሳ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ትራንስፎርመሮችን መልሶ የመተካት ሥራዎችን ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም ነው ያብራሩት።

‎በሆለታ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ አገልግሎት የሚሰጥ አንድ ባለ 500/132/33 ኪሎ ቮልት አዲስ ትራንስፎርመር የግዢ ሂደት ተጠናቆ በአሁኑ ወቅት በምርት ሂደት ላይ እንደሚገኝም ነው አቶ እስማኤል የገለፁት።

‎እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ለሰበታ 2 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ አንድ ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመር ግዥ ለመፈፀም በጨረታ ሂደት ላይ ይገኛል።

‎ለኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎቹ አዳዲስ ትራንስፎርመሮች ተገዝተው ሥራ እስኪጀምሩ ድረስ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመተባበር ነባር መስመሮችን በማስተካከል፣ የኃይል ሥርጭቱን በማመጣጠን እና ጭነትን በማዛወር የኃይል አቅርቦቱን ለማረጋጋት እንደሚሰራ አብራርተዋል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top