ተቋሙ ፕሮጀክቶችን በራሱ ፋይናንስ ለመገንባት የሚያስችል አቅም እየፈጠረ ነው

ተቋሙ ፕሮጀክቶችን በራሱ ፋይናንስ ለመገንባት የሚያስችል አቅም እየፈጠረ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በራሱ የፋይናንስ አቅም ለመገንባት የሚያስችል ቁመና ላይ መድረሱን በተቋሙ የኮርፖሬት ፋይናንስና ሀብት አስተዳደር ዘርፍ አስታወቀ፡፡

በዘርፉ የፋይናንስ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ መንግሥቱ እንዳስታወቁት የተቋሙ የፋይናንስ ቁመና በመጠናከሩ ፕሮጀክቶችን በራስ የገቢ ምንጭ የመሸፈን አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡

ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ይሰበሰባል ተብሎ ከሚጠበቀው ከ120 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ውስጥ ለኦፕሬሽን ሥራዎች የሚያወጣው ወጪ ከ20 ቢሊዮን ብር የማይበልጥ መሆኑን ገልፀው ቀሪው ለብድር ክፍያ እና ለተለያዩ የኃይል መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ እንደሚውል ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ተቋሙ በ2018 በጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት ከተለያዩ የገቢ ምንጮች ከሰበሰበው ውስጥ አብዛኛውን ለብድር ክፍያ እና ለፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ እያዋለ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት፡፡

በ2016 በጀት ዓመት ከ107 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር በላይ፣ በ2017 ወደ 178 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ከ210 ሚሊዮን ዶላር በላይ በራስ የፋይናንስ አቅም ለፕሮጀክቶች ግንባታ ማስፈፀሚያ፣ ለብድር ክፍያ እና ለኦፕሬሽን ሥራዎች ወጪ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ባለፉት አምስት ወራት በራስ የፋይናንስ አቅም ለኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ ማስፈፀሚያ ከ105 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ክፍያ መፈፀሙን አቶ አለማየሁ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ለአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከ6 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዲሁም ለባህር ዳር- ወልዲያ- ኮምቦልቻ የኃይል ማከፋፈያና ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ግንባታ ከ22 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ተሸፍኗል፡፡

ይህም ተቋሙ ከዚህ ቀደም ፕሮጀክቶችን ሙሉ በሙሉ በብድር ያስፈፅም ከነበረበት አሰራር ወጥቶ በራሱ አቅም ወደ መገንባት እየተሸጋገረ ስለመሆኑ አመላካች ነው ብለዋል፡፡

ተቋሙ በተያዘው በጀት ዓመት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ብድር ለመክፈል አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው እስካሁን ከ67 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ክፍያ መፈፀሙንም ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይም ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የብድር ወለድ መክፈሉን የገለፁት አቶ አለማየሁ የተቋሙ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እያደገ መምጣቱ፣ ከራስ ገቢ ብድርን የመክፈል ሥርዓት መዘርጋቱ እና በመንግሥት የፀደቀ የብድር መክፈያ ዕቅድ ተግባራዊ መደረጉ ለለውጡ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን አብራርተዋል፡፡

የተቋሙን የፋይናንስ ቁመና ይበልጥ ለማጠናከር የኦፕሬሽን ሥራዎችን አስተማማኝነት ማሳደግ፣ የደንበኞችን የኃይል ፍጆታ መጨመር እና ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ማጠናቀቅ እንዲሁም ተቋማዊ ሀብቶችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
‎ 
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top