የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለፉት 6 ወራት አገልግሎት ከማይሰጡ ንብረቶችን በሽያጭ በማስወገድ 82 ነጥብ 25 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን የንብረትና ጠቅላላ አገልግሎት ዘርፍ ገለጸ።
በዘርፉ የንብረት አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምራት ገብረመድህን እንደገለጹት ተቋሙ በ2018 በጀት ዓመት ከቁርጥራጭ ብረቶች፣ ካገለገሉ ተሸከርካሪዎችና ጎማዎች፣ ከበርሜሎች፣ ከኤሌክትሪክ ገመዶች፣ ከተለያዩ ባትሪዎችና መሰል ንብረቶች ሽያጭ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት አቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡
ባለፉት 6 ወራት አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶችን በማስወገድ 70 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ 82 ነጥብ 25 ሚሊዮን ብር ገቢ በመሰብሰብ የዕቅዱን 117 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት የተከናወኑ ሥራዎች ለበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት ምቹ መደላድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶችን የማስወገዱ ሥራ የመንግሥት ንብረት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 9/2003 መሰረት በማድረግ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ቀደም ሲል አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶችን ለማስወገድ የሚከናወነው ጨረታ ላይ የሚታይ ችግርን በዘላቂነት ለመቅረፍ በኦንላይን የጨረታ ሂደት ከኦክሽን ኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”