የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፋይናንስ ሥርዓት በብዙ አመላካቾች ጤናማ የሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የተቋሙ የፋይናንስ ሥራ አስፈፃሚ አስታወቁ፡፡
ሥራ አስፈፃሚው አቶ አለማየሁ መንግሥቱ እንደገለፁት የተቋሙ የፋይናንስ ሥርዓት ወደጤናማ ሥርዓት የተሸጋገረው በመንግሥት የተደረጉ ድጋፎችና በተቋሙ የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ውጤት በማስገኘታቸው ነው፡፡
የተቋሙ ዓመታዊ ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱ የአጭር ጊዜ የመክፈል አቅም (Liquidity Ratio) ማደጉን እንደሚያሳይ አቶ አለማየሁ ገልፀዋል፡፡
በ2015 በጀት ዓመት 22 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የነበረው ዓመታዊ ገቢ በ2017 በጀት ዓመት ወደ 72 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱን እንዲሁም በተያዘው በጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ አማራጮች ከ120 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ተቋሙ በጠቅላላ እና በሥራ ማስኬጃ ትርፍ (Gross and Operating Profit) ደረጃ አበረታች ለውጥ እያሳየ መምጣቱን የጠቀሱት አቶ አለማየሁ ይህም ከኃይል ሽያጭና ከሌሎች የሚገኘው ገቢ ከኦፕሬሽን ወጪ በላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ የውጭ ብድር ጫናዎችን በመቀነስ የተጣራ ትርፍ (Net Profit) ለማግኘት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ሥራ አስፈፃሚው ይህም ተቋሙ ጠንካራ የፋይናንስ ቁመና ላይ እንዲደርስ ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው አብራርተዋል፡፡
እንደ አቶ አለማየሁ ገለፃ የተቋሙን የብድር እና የሀብት መጠን ንፅፅር (Debt-to-Equity Ratio) እና ወለድ የመክፈል አቅም የሚያሳየው መለኪያ ካለፉት ዓመታት አንፃር ዕድገት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡
መንግሥት የወሰደው የብድር ሽግሽግ እርምጃ የተቋሙ ገቢ እንዲያድግ አዎንታዊ ሚና መጫወቱን የተናገሩት ሥራ አስፈፃሚው ከመደበኛው የገበያ ብድር በተሻለ በአነስተኛ ወለድ ሲሰጥ የቆየውን የብድር ዓይነት (Concessional Loan) ጨምሮ በቢሊዮን የሚቆጠር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር እንዲዛወር መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም የሕብረተሰቡን የመክፈል አቅም ያገናዘበ የታሪፍ ማሻሻያ መደረጉ፣ የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ወደ ሥራ መግባት፣ የኃይል ሽያጭ ስብጥር እና ምርታማነት እያደገ መምጣት እንዲሁም አገልግሎት የማይሰጡ የተለያዩ ንብረቶችን በማስወገድ የገቢ ማመንጫ መደረጉ ለገቢው ማደግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከታቸውን አስረድተዋል፡፡
ተቋሙ ወደ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ሥርዓት መሸጋገሩ የቋሚ ንብረቶችን ዋጋ በመከለስ የሀብት መጠኑን ከፍ ለማድረግ እንዳገዘውም ነው ሥራ አስፈፃሚው ያብራሩት፡፡
መንግስት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ የሚገኙ ግዙፍ የኃይል መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በቅርበት መከታተሉና ድጋፍ ማድረጉ በተቋሙ የፋይናንስ ቁመና ላይ አዎንታዊ ፋይዳ ማምጣቱንም አመልክተዋል፡፡
የዲጂታል የአሰራር ሥርዓት በመተግበር፣ የተቋሙ ከፍተኛ የሥራ አመራር ወቅታዊ የፋይናንስ መረጃዎችን በወቅቱ እንዲያገኙና ፈጣን ውሳኔዎችን እንዲያሳልፍ በማድረግ የፋይናንስ ሥርዓቱን ጤናማነት አስጠብቆ ለማስቀጠል እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”