ተቋሙ ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራ ትኩረት ሰጥቷል

ተቋሙ ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራ ትኩረት ሰጥቷል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን በተቋሙ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በበለጸገው የፈተና ሥርዓት አስተዳደር መተግበሪያ ላይ የልምድ ልውውጥ አካሂደዋል።

የዘርፉ ተወካይ ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ጽዮን በቀለ በልምድ ልውውጥ መድረኩ ላይ እንደገለጹት መተግበሪያው በውስጥ አቅም ለምቶ ወደ ሥራ መግባቱ ተቋሙ ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራ የሠጠውን ትኩረት ያሳያል።

መተግበሪያው በሙከራ ሂደት ደህንነቱን ከማረጋገጥ ጀምሮ አሰራሩንና ሌሎች ሂደቶችን በማለፍ ተቀባይነት በማግኘቱ እና ውጤታማ በመሆኑ ወደ ትግበራ መግባቱን ገልጸዋል።

መተግበሪያው የተቋሙ ሠራተኛ ማንኛውንም የዕድገትና ዝውውር ፈተናዎችን ባለበት ሆኖ ለመሰውድ እንደሚያስችለው ተወካይ ሥራ አስፈጻሚዋ አስረድተዋል፡፡

ይህም ወደ ዋናው ተቋም መጥቶ ለመፈተን የሚባክነውን ጊዜ እና የሚጠይቀውን ከፍተኛ ወጪ ከማስቀረት ባሻገር ከተዓማኒነትና ግልጸኝነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

መተግበሪያውን ያበለጸጉት በጀነሬሽን ቢዚነስ ዘርፍ ባለሙያ የሆኑትና አቶ ቃልአብ አየለ በበኩላቸው መተግበሪያው ሁሉንም ዓይነት ፈተናዎች በአንድ ቋት የያዘ፣ ለመረዳት ቀላል፣ የሰዎችን ጣልቃ ገብነት የሚያስቀር፣ ደህንነቱ የተጠበቀና አዋጭ መሆኑን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኢአርፒ ቴክኒካል ድጋፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ገብሬ በበኩላቸው በተቋማቸው የሚሰጡ የፈተና፣ የዕድገትና ዝውውር ሂደቶች በወረቀት በመሆኑ ሂደቱን ወደ ዲጅታል ሥርዓት ለማምጣት ከልምድ ልውውጡ ወሳኝ ግብዓት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ሥራ አስኪያጁ ስለ መተግበሪያው ጥቅምና ዝርዝር አሰራር ለተሰጣቸው ሰፊ ማብራሪያ ተቋሙን አመስግነው በቀጣይ የተገኙ ልምድና ተሞክሮዎችን ወደ ተቋማቸው ወስደው ተግባራዊ ለማድረግ በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top