ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር ለሠራተኞች ውጤታማነትና ምርታማነት ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ

ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር ለሠራተኞች ውጤታማነትና ምርታማነት ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ


‌‎በኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር ለሠራተኞች ውጤታማነትና ምርታማነት ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

‎በተቋሙ የኮርፖሬት ገቨርናንስና ኮምፕሊያንስ ዘርፍ ሥር የሚገኙ የሥራ ክፍሎች በሆለታ ባለ 500 እና በገፈርሳ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
‎‎በዚህ ወቅት በተቋሙ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መከታተያ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ደረጀ አጥናፌ  እንደገለፁት የመስክ ምልከታው በኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎቹ ውስጥ እየሰሩ የሚገኙ ሠራተኞች ያሉባቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመለየት እና  ሰላማዊና ውጤታማ የሥራ አካባቢ መኖሩን ለማረጋገጥ ያለመ ነው።

‎‎በሆለታ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የዕቃ ግምጃ ቤት እጥረት በመኖሩ ምክንያት የተቋሙ ንብረቶች ምቹና አስተማማኝ ባልሆነ ቦታ ላይ መቀመጣቸውን ገልፀው ንብረቶቹን ከብክነት ለመታደግ አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል።

‎‎በጣቢያዎቹ እየተከናወኑ ያሉ የኦፕሬሽን ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ቢሆንም ከሰው ኃይል እጥረት እና ከሥራ ላይ ደህንነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል።

‎‎የመልካም አስተዳደር ቡድኑ ድንገተኛ ጉብኝቶችን በሁሉም የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት አቶ ደረጀ የመስክ ጉብኝቶቹ ለተቋሙ ውጤታማነት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸውም ነው ያብራሩት።

‎‎በተቋሙ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሌንሴ ኢደኤ እንደተናገሩት በዋናው መሥሪያ ቤት ለሚገኙ ሠራተኞች የሚቀርቡ ፋሲሊቲዎች በሙሉ በሁሉም የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ሊመቻቹ ይገባል።

‎‎የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሥራ አካባቢ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መሆን እንዳለባቸው ጠቅሰው የመፀዳጃ ቤት እና የንፁህ ውሃ መጠጥ አቅርቦት ችግሮችም ሊቀረፍ እንደሚገባ ገልፀዋል።

‎‎በተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን በበኩላቸው የኦፕሬሽን ሠራተኞች የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች በመቋቋም ሥራቸውን በአግባቡ የማከናወን የሥራ ባህል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

‎‎ተቋሙ በሀገሪቱ ካሉ ግዙፍ ንብረት ካላቸው ተቋማት ግንባር ቀደም መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ይሁን እንጂ በኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ውስጥ ያለው የንብረት አያያዝ እና አወጋገድ ሥርዓት በጥብቅ ሊፈተሽ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

‎‎ለሥራ የሚያገለግሉ ንብረቶችን በመለየትና ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ እንዲሁም የማይፈለጉትን በፍጥነት የማስወገድ ሥራ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልፀው ይህም የተቋሙን ሀብት በአግባቡ ለመቆጣጠርና ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።

‎‎በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ ሳቢ እና ከልማት ሥራዎች ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ ለማድረግ በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎች በትኩረት እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

‎በተቋሙ የህግ አገልግሎት መምሪያ ዳይሬክተር ወ/ሮ መስከረም በቀለ እንደገለፁት በመስክ ምልከታው የተለዩትን ችግሮች ለመፍታትና የተቋሙን ውጤታማነት ለማሳደግ የኮርፖሬት ገቨርናንስና ኮምፕሊያንስ ዘርፍ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top