የኃይል ማመንጫ ጣቢያውን ወደ ሥራ ለመመለስ የሚያስችሉ የጥገና ሥራዎች እየተከናወኑ ነው

የኃይል ማመንጫ ጣቢያውን ወደ ሥራ ለመመለስ የሚያስችሉ የጥገና ሥራዎች እየተከናወኑ ነው

የጢስ ዐባይ 1 የኃይል ማመንጫ ጣቢያን ዳግም ወደ ሥራ ለመመለስ የሚያስችሉ የጥገና ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የጀነሬሽን ቢዝነስ ዘርፍ አስታወቀ፡፡

በዘርፉ የጀነሬሽን ቴክኒካል ድጋፍ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ተስፋዬ እንዳስታወቁት ጣቢያው በመለዋወጫ ዕቃዎች እጥረት እና በከፍተኛ የደለል ክምችት ምክንያት ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት መስጠት አቁሞ ቆይቷል፡፡

ጣቢያው ከጢስ ዐባይ 2 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ጋር የጋራ የውሃ ማስገቢያ በር (Intake gate) የሚጠቀም መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ይሁን እንጂ የራሱ መከላከያ በር የሌለው በመሆኑ የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦው በደለል ተዘግቶ መቆየቱን ገልፀዋል።

በዚህም በጣቢያው የሚገኙ አመራሮችና ሠራተኞች ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ በቱቦው ውስጥና በታችኛው የወንዝ አቅጣጫ እንደ ኮንክሪት ጠንክሮ የነበረውን የደለል ክምችት ማፅዳት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ በጣቢያው ሁለት ዩኒቶች ላይ የኤሌክትሮና የሃይድሮ ሜካኒካል የጥገና ሥራዎችን በማከናወን ተርባይኖችን የማሽከርከር ሙከራ (Idle Run) ደረጃ ላይ ማድረስ ተችሏል፡፡

ጣቢያው ለረጅም ጊዜ ከአገልግሎት ውጭ ሆኖ በመቆየቱ ምክንያት የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎቹ ለሌሎች የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በመለዋወጫ መልክ ተወስደው እንደነበር የጠቆሙት አቶ ዮናስ በአሁኑ ወቅት ግን ዕቃዎቹን በመመለስ ዳግም የመገጣጠም ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ጣቢያው በትንሽ ውሃ ከፍተኛ ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ቀሪ የመቆጣጠሪያ እና የትራንስፎርመር ዘይት ማጣራት ሥራዎች እንደተጠናቀቁ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ተርባይኖቹን የማሽከርከር ሙከራ ደረጃ ላይ ቢደርስም ከባህርዳር ከተማ ጋር የሚያገናኘው የ45 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በእርጅና እና በስርቆት ምክንያት በመጎዳቱ የሚመነጨውን ኃይል ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ ተጨማሪ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ ገልፀዋል።

ሥራው ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም በመከናወኑ ጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራርና የዕውቀት ሽግግር ስለተገኘበት የተቋሙ ሥራ አመራር ላደረገው አዎንታዊ ድጋፍ እንዲሁም በጥገናው ላይ ለተሳተፉ ባለሙያዎች በሙሉ ዳይሬክተሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ዘርፉ በሀገሪቱ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት አስተማማኝነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ነባር የኃይል ማመንጫ ሀብቶችን ዳግም በማልማት የኃይል አማራጮችን ለማስፋት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

በ1956 ዓ.ም ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የጢስ ዓባይ 1 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ በወቅቱ ለባህር ዳር ጨርቃጨርቅ ፋብሪካና ለከተማዋ የኢንዱስትሪ ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንዲጫወት ታስቦ የተገነባ አንጋፋ ጣቢያ ነው።

ጣቢያው በአጠቃላይ 12 ነጥብ 6 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን እያንዳንዳቸው 4 ነጥብ 2 ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችሉ ሦስት ፍራንሲስ ተርባይኖችም አሉት።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top