ተቋርጦ የቆየው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዳግም አገልግሎት መስጠት ጀምሯል

ተቋርጦ የቆየው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዳግም አገልግሎት መስጠት ጀምሯል

በአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ በስርቆት ምክንያት ተቋርጦ የቆየው የቆቃ- አዋሽ 7 ኪሎ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዳግም አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የማዕከላዊ 2 ሪጅን አስታወቀ።

የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ዘበርጋ እንዳስታወቁት በ14 የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ በተፈፀመ የስርቆት ወንጀል ምክንያት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ከአገልግሎት ውጭ ሆኖ ቆይቷል፡፡

በስርቆቱ ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ዳግም ለመመለስ 14 የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎችን መልሶ የመትከል ሥራ መሰራቱን ገልፀዋል፡፡

ለሦስት ወራት ያህል በበረሃማው የአዋሽ ፓርክ ውስጥ ሲከናወን የቆየው ይህ የጥገና ሥራ የ11 ኪሎ ሜትር የኮንዳክተር ሽቦ ዝርጋታን ያካተተ እንደነበረም ነው ያብራሩት፡፡

የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ መጠገን ወደ ምስራቁ የሀገራችን ክፍል እና ወደ ጅቡቲ የሚላከውን የኃይል አቅርቦት አስተማማኝ እንደሚያደርገው የገለፁት ዳይሬክተሩ አንዱ መስመር ቢቋረጥ በሌላኛው በኩል የኃይል አቅርቦቱን ለማስቀጠል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።

የጥገና ሥራው የተከናወነው በሪጅኑ የሰው ኃይል መሆኑን የጠቀሱት አቶ አለማየሁ ይህም የጥገና ባለሙያዎቹ የአካባቢውን አስቸጋሪ የአየር ንብረት ተቋቁመው ሥራውን ማከናወናቸው በቀጣይ ለሚሰሩ ተመሳሳይ ሥራዎች ትልቅ ልምድና አቅም የተገኘበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በሪጅኑ የማስተላለፊያ መስመሮች ጥገና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጎሳዬ ደምሴ በበኩላቸው በኃይል ማስተላለፊያ የብረት ምሰሶዎች ላይ የሚፈፀሙ የስርቆት ወንጀሎችን ለመከላከል የተቋሙ ደህንነትና አስተዳደራዊ ጉዳዮች መምሪያ ከአፋር ክልል የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢው ማህበረሰብ በጥበቃ ሥራው ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀም ስርቆት በሀገር ኢኮኖሚና በኃይል አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የገለፁት ሥራ አስኪያጁ የአካባቢው መስተዳድርና ማህበረሰብ የመስመሩን ደኅንነት ከስርቆትና ከጥቃት በመጠበቅ ረገድ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የቆቃ- አዋሽ 7 ኪሎ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር የጥገና ሥራ በስኬት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ርብርብ ላደረጉ የጥገና ባለሙያዎች፣ ለአዋሽ ከተማና ለአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ አስተዳደሮች፣ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም ለፌዴራል ፖሊስ አባላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top