የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አሜአ ፓወር ከተሰኘ የተባበሩት አረብ ኢሜሬቶች ኩባንያ ጋር የኃይል ግዥ ሥምምነት ተፈራረመ።
የአይሻ 1 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ትግበራ ይፋ ለማድረግ በተዘጋጀው የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ላይ አልሚው አሜአ ፓወር ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር የፕሮጀክት ትግበራ አጋርነት እንዲሁም ከሶማሌ ክልል መንግስት ጋር የመሬት ሊዝ ሥምምነት ተፈራርሟል።
የኃይል ግዢ ሥምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እና በአሜአ ፓወር ኩባንያ የአይሻ 1 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ራጂሽ ራሚሽ ተፈራርመዋል።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ዘርፍ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፓሊሲ ትግበራ መገባቱን የገለፁት ሚኒስትሩ በዘርፉ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንደ አቶ አህመድ ገለፃ የአይሻ 1 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ እና የተባበሩት አረብ ኢሜሬቶች ከዚህ ቀደም በተለያዩ መስኮች ያላቸውን ሁሉን አቀፍ ትብብርና ግንኙነት የሚያጠናክር ነው።
ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን እያከናወነቻቸው ላሉ ተግባራት ማሳያ እንደሆነም ነው አቶ አህመድ የገለፁት።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አቅሟን ለማጠናከር በነደፈቻቸው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ የኢንዱስትሪ እና የከተሞች መስፋፋት ዕቅዶች ፈጣን ለውጥ እያስመዘገበች ትገኛለች።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሦስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ቀርፆ ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።
የአይሻ 1 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የዚሁ ዕቅድ አካል መሆኑንም ተናግረዋል።
እንደ ኢንጂነር አሸብር ገለፃ ሥምምነቱ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ላይ መሰረት ላደረገ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ስትራቴጂዋ ተጨማሪ ግብዓት ይሆናል።
የንፋስ ኃይል ማመንጫ ግንባታው ሲጠናቀቅ በዓመት በአማካኝ 1 ሺህ 261 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል እንደሚያመነጭም ነው የጠቀሱት።
በአሜአ ፓወር የአይሻ 1 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ራጂሽ ራሚሽ በበኩላቸው የተባበሩት አረብ ኢሜሬቶች ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ለ1 ሺህ 500 ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ያሉት ሥራ አስኪያጁ ኃይል ማመንጨት በሚጀምርበት ወቅትም ከ4 ሺህ በላይ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።
በገንዘብ ሚኒስቴር የመንግሥትና የግል አጋርነት ቦርድ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አበበ ገ/ህይወት በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በዓመት 690 ቶን የካርበን ልቀትን የማመጣጠን አቅም አለው።
ከኩባንያው ጋር የተደረገው ሥምምነት ከፕሮጀክት ሥምምነት በላይ አድርገን የምናስበውና ለቀጣይ ኢንቨስትመንት መሰረት የሚጥል ነውም ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በመንግሥት እና የግል አጋርነት ማዕቀፍ በ620 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚገነባ ትልቅ ኢንቨስትመንት እንደሆነም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የጠቆሙት።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሸዴን ጨምሮ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዴኤታዎች፣ የመንግሥትና የግል አጋርነት ቦርድ አባላትና የጽ/ቤት ሠራተኞች፣ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ተወካዮች፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶ ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተርና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች፣ የተባበሩት አረብ ኢሜሬቶች ከፍተኛ የመንግሥትና የአሜአ ፓወር የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”















