የአይሻ አንድ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በቀጣይ ለሚተገበሩ የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶች ማሳያ መሆን እንደሚችል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አስታወቁ።
ተቋሙ አሜአ ፖወር ከተሰኘው የተባበሩት አረብ ኢመሬቶች ኩባንያ ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ግዥ ሥምምነት ሲፈራረም ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንደተናገሩት ሥምምነቱ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ንፁህና ታዳሽ የኃይል ማዕከል ለመሆን ካላት ራዕይ ጋር የሚጣጣም ነው።
መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፉ፣ ለኮሪደር ልማቱ እና ለጤናማ የኑሮ አካባቢዎች መስፋፋት ትኩረት በመስጠቱ ምክንያት የኃይል ፍላጎት እያደገ መምጣቱን ኢንጂነር አሸብር ተናግረዋል።
የኢነርጂ ዘርፉ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት መፋጠን፣ የኑሮ ደረጃ መሻሻልና ለዘላቂ የልማት ግቦች መሳካት ከፍተኛውን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝም ነው የጠቆሙት።
ተቋሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ለመጣው የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት በርካታ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ኢንጂነር አሸብር ገለፃ ኢትዮጵያ ለታዳሽ ኃይል ባላት ቁርጠኝነት መሠረት በንፋስ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ላይ በንቃት እየተሳተፈች ነው።
የአይሻ 1 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የዚሁ ዕቅድ አካል መሆኑንም ነው የገለፁት።
ሥምምነቱ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ላይ መሰረት ላደረገ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ስትራቴጂዋ ተጨማሪ ግብዓት ይሆናል ብለዋል።
የንፋስ ኃይል ማመንጫ ግንባታው ሲጠናቀቅ በዓመት በአማካኝ 1 ሺህ 261 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል እንደሚያመነጭም ነው የጠቀሱት።
በታዳሽ ኃይል ልማት፣ ግንባታና አስተዳደር ዘርፍ የተሰማራው አሚአ ፓወር በአይሻ አንድ የንፋስ ኃይል ማመንጫ 300 ሜጋ ዋት በማመንጨት ለ25 ዓመታት ለኢትዮጵያ ለመሸጭ ነው ሥምምነቱን የፈረመው።
ሥምምነቱ ከዳር እንዲደርስ ላደረጉት አካላት ምስጋናቸውን ያቀረቡት ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጥረቱ በትብብርና በጋራ የማደግን አስፈላጊነት ያሳየ ነው ብለዋል።
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”









