የቡኢ ማከፋፊያ ጣቢያ የከተማዋንና የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊ እድገት እያፋጠነ መሆኑን የቡኢ ከተማ አስተዳደር ገለጸ።
የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ በለጠ ጫካ እንደገለጹት የቡኢ ማከፋፊያ ጣቢያ ከመገንባቱ በፊት ከተማዋ የኃይል አቅርቦት ከቡታጅራ ማከፋፊያ ጣቢያ ስታገኝ የነበረ ሲሆን ይህም በከተማዋና አካባቢው የሚመጡ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ እንቅፋት ፈጥሮ ቆይቷል።
የቡኢ ባለ 132 ማከፋፊያ ጣቢያ ከተገነባ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ግን የአካባቢው የኢንቨስትመንት ፍሰት እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
በዚህም ከፍተኛ ኃይል የሚጠይቁ ከ40 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ወስደው 6ቱ ወደ ማምረት ሲገቡ ቀሪዎቹ ደግሞ በግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
አሁንም በከተማውና አካባቢው ያለውን አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ከግምት ውስጥ በማስገባት በርካታ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑንም አቶ በለጠ አብራርተዋል።
የአካባቢውን የመልማት አቅምና ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር በማድረጉ አመስግነዋል።
የቡኢ ማከፋፍያ ጣቢያው የኦፕሬሽን ባለሙያ አቶ አይሸሹም አበረ በበኩላቸው የማከፋፍያ ጣቢያው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 4 ከተሞችና 3 ወረዳዎች እንዲሁም አጎራባች የኦሮሚያ ክልል ወረዳዎችን የኃይል ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸዋል።
ጣቢያው 45 ሜጋ ዋት የመጫን አቅም ያለው ሲሆን አሁን በጥቅም ላይ የዋለው ዘጠኝ ከመቶው ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም ቡኢ ከተማን ጨምሮ በአካባቢው በመገንባት ላይ ለሚገኙ ፋብሪካዎችም ሆነ በቀጣይ ለሚመጡ ኢንቨስትመንቶች የኃይል አቅርቦት ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስ የሚያስችል አቅም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”