ለወርቅ ማዕድን ማምረቻ ፕሮጀክት ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

ለወርቅ ማዕድን ማምረቻ ፕሮጀክት ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከኩርሙክ የወርቅ ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እና የኩርሙክ ወርቅ ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብሮክስ ወርቁ ተፈራርመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትክ ኃይል የገበያና ቢዝነስ ልማት መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሕይወት እሸቱ ስምምነቱን አስመልክተው እንደተናገሩት ከኩባንያው ጋር የተካሄደው ስምምነት ለ12 ዓመታት የሚቆይና 35 ሜጋ ዋት ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል ነው፡፡

የኃይል አቅርቦት ስምምነት ክፍያው በዶላር እንደሚፈፀም ገልፀው ይህም የተቋሙን የውጭ ምንዛሬ በማሳደግ በኩል ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡

እንደ አቶ ሕይወት ገለፃ ስምምነቱ ከኃይል አቅርቦት ባለፈ ለወርቅ ማምረቻ ፕሮጀክቱ ኃይል ለማቅረብ የሚያግዘውን የኃይል ማስተላለፊያ መስመር የዲዛይን እና የግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ለተቋሙ ተጨማሪ ገቢ የሚያገኝበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡

ይህም ተቋሙ በኃይል መሰረተ ልማቶች ግንባታ ሥራ ላይ ያለውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ በሀገሪቱ እየተከናወኑ ለሚገኙ የተለያዩ ዘርፎች አስተማማኝ ኃይል በማቅረብ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን በመደገፍ ሃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝም ተመላክቷል፡፡

የኩርሙክ ወርቅ ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ብሮክስ ወርቁ በበኩላቸው ከተቋሙ ጋር የተደረገው ስምምነት ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ ለኩባንያው እንደ ትልቅ ስኬት የሚቆጠር ነው ብለዋል፡፡

ስምምነቱ ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ ሲገባ አስተማማኝ ኃይል ለማግኘት እንደሚያስችለው ጠቅሰው ተቋሙ በስምምነቱ መሰረት ኃይል ማቅረብ እንደሚኖርበትም አስገንዝበዋል፡፡

የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካውን በ2018 ዓ.ም ወደ ሥራ ለማስገባት ዕቅድ እንደተያዘለት የተናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ በአሁኑ ወቅትም ለፕሮጀክቱ ግንባታ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ወደ ቦታው የማጓጓዝ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ዘጠኝ ቶን የሚጠጋ ወርቅ የማማረት አቅም ይኖረዋል የተባለው እና የ500 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት እንደሆነ የተነገረለት ይህ የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ኩርሙክ ወረዳ የሚገነባ መሆኑንም አቶ ብሮክስ ተናግረዋል፡፡

የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካው ተጨማሪ የኃይል ፍላጎት ሲኖረው በአቅርቦቱ እና በዋጋው ላይ ማሻሻያ እንደሚደረግበት በውሉ ላይ መካተቱንም የሥራ ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡

“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top