በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በብር 20 ቢሊዮን እና በደላር ደግሞ140 ሚሊዮን ገቢ ተገኝቷል

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በብር 20 ቢሊዮን እና በደላር ደግሞ140 ሚሊዮን ገቢ ተገኝቷል

በ2016 በጀት ዓመት ከተለያዩ የገቢ ምንጮች በብር 20 ቢሊዮን እና በዶላር ደግሞ 140 ሚሊዮን ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አስታወቁ።

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ የተቋሙን የ2016 በጀት ዓመት የፕሮጀክት፣ የኦፕሬሽን እና የገቢ አፈፃፀምን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚው በመግለጫው እንዳመለከቱት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴን ግድብን ጨምሮ 7 ሺህ 242 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው አምስት የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች በግንባታ ላይ ይገኛሉ ።

በግንባታ ላይ ካሉት ፕሮጀክቶች መካከል የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና የአይሻ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በተወሰኑ ዩኒቶቻቸው ኃይል ማመንጨት መጀመራቸውንም  ጠቁመዋል።

ከማመንጫ ጣቢያዎች በተጨማሪ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

እንደ ኢንጂነር አሸብር ገለፃ በበጀት ዓመቱ የኃይል ማመንጫዎች የግንባታ አፈፃፀም ከ76 በመቶ በላይ እንዲሁም የማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያዎች አፈፃፀም በአማካኝ 86 በመቶ ማከናወን ተችሏል።

በ2016 በጀት ዓመት 20 ሺህ 974 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ታቅዶ  20 ሺህ 522 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል በማመንጨት የዕቅዱን 98 በመቶ ማሳካት እንደተቻለም ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥ 96 በመቶ ከውሃ፣ 3 ነጥብ 3 በመቶ ከንፋስ እንዲሁም 0 ነጥብ 2 በመቶው ደረቅ ቆሻሻ በማቃጠል የመነጨ መሆኑን ገልፀዋል።

በበጀት ዓመቱ ከመነጨው ኃይል ጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ጣቢያ የ34 በመቶ፣ ህዳሴ የ17 በመቶ  እንዲሁም በለስ የ 9 ነጥብ 6 በመቶ ድርሻ እንደነበራቸውም በመግለጫው ጠቁመዋል።

የተቋሙ ኃይል የማመንጨት አቅም ባለፉት ስድስት ዓመታት በአማካኝ በስምንት በመቶ እየጨመረ ስለመሆኑም ተነስቷል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንዳሉት ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ከሀገር ውስጥና ከውጭ የኃይል ሽያጭ፣ ከፋይበር ኦፕቲክስ ኪራይ፣ አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶችን በማስወገድ እና ለሦስተኛ ወገን የማማከርና የግንባታ ሥራዎን በማከናወን ገቢ እያገኘ ይገኛል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ለሀገር ውስጥ በብር ከተሸጠ ኃይልና ከሌሎች አገልግሎቶች 19 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅድ 20 ቢሊዮን ብር  የተገኘ ሲሆን ለውጭ ሀገራት ኤክስፖርት ከተደረገ ኃይል እና ከዳታ ማይኒንግ የኃይል አቅርቦት ደግሞ 140 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።

ይሁንና ለሱዳን እና ለጅቡቲ የቀረበው ኃይል በመቀነሱ ምክንያት ከኃይል ኤክስፖርት የተገኘው ገቢ አፈፃፀም ከዕቅዱ የ26 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ነው ያስታወቁት።

ኢንጂነር አሸብር በመግለጫቸው እንዳነሱት ተቋሙ በበጀት ዓመቱ  በሀገር ውስጥ በዳታ ማይኒንግ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች ካቀረበው ኃይል 27 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ በማግኘት የዕቅዱን 97 በመቶ ማሳካት ተችሏል።

ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ የተቋሙ ገቢ በአማካኝ በ34 በመቶ ዕድገት እያሳየ መሆኑን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈፃሚው የገቢ አሰባሰቡም በየዓመቱ እየተሻሻለ እንደሚገኝ ነው ያነሱት።

በዚህም የ2016 በጀት ዓመት የገቢ አሰባሰብ ከ2015 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ17 በመቶ እድገት ያለው መሆን ዋና ሥራ አስፈፃሚው በማሳያነት አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱ የታቀዱ ሥራዎችን ለማከናወን በማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ እየተፈፀመ ያለው ስርቆትና የፀጥታ ችግሮች ፈተና ሆነው እንደነበር ኢንጂነር አሸብር ተናግረዋል።

“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top