ከሃገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ጋር የተጣጣመ የኃይል አቅርቦት ሪፎርም እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ

ከሃገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ጋር የተጣጣመ የኃይል አቅርቦት ሪፎርም እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን የ2016 አፈፃፀም እና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ገምግሟል።

የተቋሙን የ2016 በጀት ዓመት አፈፃፀም ያቀረቡት አቶ አሸብር ባልቻ እንደገለፁት ከ7ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የማመንጨት አቅም ያላቸው የአምስት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው።

ተቋሙ በበጀት ዓመቱ 20 ሺህ 522 ጊጋ ዋት ሰዓት ማመንጨት የቻለ ሲሆን የዕቅዱን 97 ነጥብ 8 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

ከሰው ኃይል አቅም ግንባታ አንፃር ከ2 ሺህ ለሚልቁ የተቋሙ ሠራተኞች ሙያዊ እና የአመራር ክህሎት ስልጠና መሰጠቱንም ነው ያስታወቁት።

በበጀት ዓመቱ ከሀገር ውስጥ እና ከኃይል ኤክስፖርት ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ በማግኘት የዕቅዱን 97 በመቶ ማሳካት ተችሏል ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው የተቋሙ የ2016 በጀት ዓመት አጠቃላይ አፈፃፀም 90 ነጥብ 23 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል።

በግምገማው ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ሰመሪታ ሰዋሰው ሀገሪቱ ከምትፈልገው የኃይል ፍላጎት ጋር የተጣጣመ የኃይል ዘርፍ ሪፎርም ማከናወን ይገባል ብለዋል።

ተቋሙ ከኃይል ሽያጭ፣ ገቢን ከማሳደግ እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር የኃይል ትስስር ከመፍጠር አንፃር አበረታች ሥራዎች ያከናወነ መሆኑን ሚኒስትር ዲኤታዋ ገልፀዋል::

ተቋሙ ሊያጋጥሙት የሚችሉ ስጋቶችን ቀድሞ በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚገባው የተናገሩት ደግሞ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ኃ/ሚካኤል ናቸው፡፡

የኃይል መሠረተ ልማት ስርቆትን ከመሰረቱ እልባት ለመስጠት ከክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጋር ዘላቂ ግንኙነት በመፍጠር በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ነው አቶ ሀብታሙ ያስታወቁት፡፡

ከተጠናቀቀው የበጀት ዓመት አፈፃፀም በተጨማሪ የተቋሙ የ2017 በጀት ዓመት የፊስካል እና የበጀት ዕቅድ ቀርቦ አስተያየት እና ግብአት ተሰጥቶበታል፡፡

“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top