
ስርቆትን ለመከላከል ሚዲያዎች ግንዛቤ ፈጠራ ላይ በትኩረት እንዲሰሩም ጥሪ ቀርቧል
በ2016 የበጀት ዓመት በኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ በተፈፀመ ስርቆት ተቋሙ 817 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንደደረሰበት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አስታወቁ።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው ኢንጅነር አሸብር ባልቻ የ2016 በጀት ዓመት አፈፃፀምን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት በሁሉም ክልሎች በሚገኙ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ ስርቆት በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈፀመ ይገኛል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተለያዩ ምክንያቶች ከወደቁ 74 የመስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች 57ቱ በስርቆት ምክንያት እንደወደቁ ጠቁመው እነዚህን መልሶ ለመጠገን ተቋሙ 114 ሚሊዮን ብር ወጭ እንዳደረገም አስረድተዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ የማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ በተፈፀመ ስርቆት ተቋሙ በአጠቃላይ የ817 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ደርሶበታል።
በታወሮች ላይ እየተፈፀመ ያለው ስርቆት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ተቋሙ በጥገና ሥራ ላይ እንዲጠመድ እያደረገው መምጣቱን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጠቅሰዋል።
ይህም የኃይል ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተከናወነ ባለው ሥራ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ኢንጂነር አሸብር ተናግረዋል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንዳሉት በመሠረተ ልማቱ ላይ የሚፈፀሙ ስርቆቶች ተቋሙን ለኪሳራ ከመዳረጋቸውም ባለፈ የኦፕሬሽን ሥራዎችን በማስተጓጎል ለህብረተሰቡ አስተማማኝና ጥራት ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳይቀርብ እያደረገ ይገኛል።
ከዚህም ሌላ በግንባታ ላይ ባሉ መስመሮች ላይ እየተፈፀመ ያለው ስርቆት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው መርሃ ግብር ተጠናቀው ወደ አገልግሎት እንዳይገቡ እያደረጋቸው ስለመሆኑም ገልፀዋል።
ስርቆትን ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎች ቢከናወኑም መስመሮቹ የሚያልፉበት መልከዓ ምድር አስቸጋሪ በመሆኑ ውጤት ማምጣት አልተቻለም ብለዋል።
ስርቆትን ለመከላከል መስመሮቹ በሚያልፉበት አካባቢ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ እና ይህን በመገንዘብ እያንዳንዱ ቀበሌ በአካባቢው ያሉ መሠረተ ልማቶችን በኃላፊነት እንዲጠብቅ የሚያደርግ አሰራር ለመዘርጋት ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑም ኢንጂነር አሸብር አመልክተዋል ።
ፕሮጀክቶቹ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩና ተጨማሪ ፕሮጀክቶችን በመገንባት የኤሌክትሪክ ኃይልን በመላ ሀገሪቱ ለማዳረስ ሁሉም ህብረተሰብ በአካባቢው ለሚገኙ የኃይል መሠረተ ልማቶች ጥበቃ ማድረግ እንዳለበት ዋና ሥራ አስፈፃሚው አሳስበዋል።
መገናኛ ብዙኃንም መሰረተ ልማቱ ለሀገር ስለሚኖረው ፋይዳ እና ስርቆቱ በሀገር ኢኮኖሚና በህብረተሰቡ ላይ እያሳደረ ስላለው ተፅዕኖ ግንዛቤ በመፍጠር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቀርበዋል።
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



