
ኢትዮጵያ በመጪው መስከረም ወደ ታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት ማድረግ የሚያስችል ቴክኒካዊ ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ አስታወቁ፡፡
ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንደገለፁት የተቋሙን ገቢ ለማሳደግ በሀገር ውስጥ የኃይል ሽያጭ እየተከናወኑ ካሉ ሥራዎች በተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ተቋሙ የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ቋት የመሆን ራዕይ በመያዝ ኃይል እያቀረበላቸው ካሉ ሀገራት በተጨማሪ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ትስስር ለመፍጠር እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ከታንዛኒያ ጋር ትስስር ለመፍጠር በተቋማቱ ደረጃ የሚከናወኑ ቴክኒካል ሥራዎች እንደተጠናቀቁ ጠቅሰው ከኬኒያ – ታንዛኒያ ያለው የማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ፍተሻ በዓመቱ መጨረሻ ሊከናወን እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ በኩልም ሽያጩ ከዚህ በፊት በተገነባው የኢትዮ -ኬንያ ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እንደሚከናወን ኢንጂነር አሸብር ገልፀዋል፡፡
ለታንዛኒያ በቀጣዩ መስከረም ወር አጋማሽ የኃይል ሽያጭ ሙከራ ሊጀመር እንደሚችል ጠቁመዋል።
በቀጣይ ከደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊ ላንድና ሱማሊያ ጋር ትስስር ለመፍጠር መታቀዱንና ሀገራቱም የኃይል ግዢ ፍላጎት ማሳየታቸውን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ተቋሙ ለሱዳን ያቀርብ የነበረውን 200 ሜጋ ዋት መቀነሱን ኢንጂነር አሸብር ገልፀዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ የሱዳን ሲስተም በሙሉ አቅሙ የሚቀርብለትን ኃይል መቀበል ስለማይችል የኃይል አቅርቦቱ ተቀንሶ ከ20 እስከ 30 ሜጋ ዋት ብቻ እየቀረበ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ለሱዳን ስታቀርብ የነበረውን የኃይል መጠን በመቀነሷ በተቋሙ ገቢ ላይ ምንም ዓይነት ስጋት እንደማይፈጥርና የሚመነጨውን ኃይል ለመጠቀም አዳዲስ የገቢ ምንጮች ታሳቢ እየተደረጉ እንደሚገኙ ኢንጅነር አሸብር አንስተዋል፡፡
የዳታ ማይኒንግ የኃይል አቅርቦት፣ ከታንዛንያ ጋር ትስስር ለመፍጠር እየተሰራ ያለውን ሥራ እና ከኬንያ ጋር የተደረገው ተጨማሪ የኃይል ትስስርንም በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለፃ በሱዳን ያለው ችግር እስኪፈታ ድረስ በአሁኑ ወቅት እየቀረበ ባለው አግባብ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ታዳሽ ኃይል በማቅረብ በቀጠናው የአረንጓዴ ትስስርን ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራች ስለመሆኗ ኢንጂነር አሸብር ተናግረዋል፡፡
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


