የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች በተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት በአንድ ጀምበር 6 መቶ ሚሊየን ችግኞች ተከላ ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፈዋል::
በመርሃ ግብሩ ላይ የተለያየ ዝርያ ያላቸው ከ1 ሺህ 700 በላይ ችግኞች መተከላቸውን በተቋሙ የዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ ተናግረዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለፃ በተቋሙ የተካሔደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር እንደ ሀገር በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተጀመረው ንቅናቄ አካል ነው፡፡
ከተተከሉት ችግኞች መካከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ለምግብነት የሚውሉ መሆናቸውንም ነው አቶ ሙላት የገለፁት፡፡
የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የተቋሙ ሥራ አመራር ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው መሆኑን የጠቆሙት የጽ/ቤት ኃላፊው ከ700 በላይ የዋና መስሪያ ቤት ሠራተኞች የተሳተፉበት እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
የታዳሽ ኃይል አማራጮችን በመጠቀም አረንጓዴ እና ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሁሉም የኃይል ማመንጫዎች፣ ማከፋፈያ ጣቢያዎች እና በሪጅን ቢሮዎች የችግኝ ተከላ እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡
አረንጓዴ አሻራን ማኖር ለቀጣይ ትውልድ ትልቅ ትሩፋት መሆኑን የገለፁት አቶ ሙላት የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች ንቅናቄው ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ችግኞችን በመትከል አሻራቸውን በማኖራቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በተመሳሳይ ዜና የሠመራ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ሠራተኞችና የሪጅኑ የሥራ መሪዎች በማከፋፈያ ጣቢያው ጊቢ ውስጥ የችግኝ ተከላ አከናውነዋል፡፡
በችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ ላይ የተሳተፉት የሰሜን ምስራቅ ሪጅን 2 ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀሰን መሀመድ እንደተናገሩት ተቋሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ባለው የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ላይ በስፋት እየተሳተፈ ይገኛል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራሙ በሪጅኑ በሚገኙት በድቼቶና አፍዴራ ማከፋፈያ ጣቢያዎች መካሄዱንም ነው የተናገሩት፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጅ ገለፃ አካባቢዉ በረሀማ በመሆኑ የሚተከሉት ችግኞች በማከፋፈያ ጣቢያዎቹ ሙቀት ለመካለከል ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የተሳተፉት የሠመራ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ኃላፊ አቶ እንድሪስ አህመድ በበኩላቸው ችግኞቹን መትከል ብቻ ሳይሆን ለፍሬ እስኪበቁ ድረስ መንከባከብም እንደሚገባ አሳስበዋል።
“ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”























