የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝነት ለማሳደግ የታሪፍ ድርድር ማዕቀፍን ማዘመን ወሳኝ ነው

የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝነት ለማሳደግ የታሪፍ ድርድር ማዕቀፍን ማዘመን ወሳኝ ነው

በኢትዮጵያ ጠንካራ የፋይናንስ አቅም በመፍጠር የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝነት ለማሳደግ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ድርድር ማዕቀፍን ማዘመን ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።

የደቡብ ኮሪያ መንግሥት የባለሙያ ድጋፍ በማድረግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን የኤሌክትሪክ ታሪፍ ድርድር ማዕቀፍን ለማዘመን ያከናወነውን ጥናት ለተቋሙ አመራሮች በስካይ ላይት ሆቴል አቅርቧል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚን በመወከል የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የትራንስሚሽን ቢዝነስ ዘርፍ ተወካይ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ደስታዓለም ኃይሉ እንደገለጹት ተቋሙ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ለማረጋገጥ የፋይናንስ አቅሙን ማጠናከርና የእውቀት ሽግግር ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

በደቡብ ኮሪያ መንግሥት ድጋፍ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን የታሪፍ ድርድር ማዕቀፍን ለማዘመን የተከናወነው ጥናት የተቋሙን የፋይናንስ አቅም በማጠናከር እና ከደንበኞች ጋር መተማመን በመፍጠር በኩል ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አብራርተዋል።

ተቋሙ በጥናቱ የተገኙ ውጤቶችንና የሚሰጡ ምክረ ኃሳቦችን ወደ መሬት በማውረድ  ውጤት ለማስመዝገብ ቁርጠኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በዘርፉ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ከደቡብ ኮሪያ መንግስት ጋር ከዚህ ጥናት ባሻገር በሌሎች ጉዳዮችም ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በኮሪያ ንግድና ኢንሸስትመንት ፕሮሞሽን ኤጀንሲ የዕውቀት ሽግግር ፕሮግራም (Knowledge Sharing Program) ከፍተኛ አማካሪ ሚስተር ሲዩንግ ቹል ሊ የኤጀንሲው የአዲስ አበባ ቢሮ ጥናቱን በማስተባበር በኩል ከፍተኛ ሚና ሲጫወት መቆየቱን ተናግረዋል።

ጥናቱ ከደቡብ ኮሪያ ልምድ በመነሳት የተቋሙን የኤሌክትሪክ ታሪፍ ድርድር ማዕቀፉን ለማዘመንና ጠንካራ የፋይናንስ አቅም ለመፍጠር የሚያስችል ግኝትና ምክረ ሀሳብ አካቶ የዕውቀት ሽግግርን ባረጋገጠ አግባብ የተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ ጊዜያዊ ጉዳይ አስፈጻሚ ሚስ ያንግ ሚ ካንግ በበኩላቸው አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ሁሉን አቀፍ እድገት ለማስመዝገብና ወደ ኢንደስትራላይዜሽን ለመሸጋገር ወሳኝ ነው ብለዋል።

የደቡብ ኮሪያ መንግስትም የኃይል አቅርቦቱን አስተማማኝነት ለማረጋገጥ በጥናትና በዕውቀት ሽግግር ከተቋሙ ጋር አብሮ በመስራቱ ደስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ደቡብ ኮሪያ በቀጣይም የኃይል ልማት ዘርፍን ለማሳደግና ለማዘመን በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሽያ ጥናት ፕሮጀክት በደቡብ ኮሪያ መንግሥት በሚደገፈው የዕውቀት ሽግግር ፕሮግራም ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከቀረቡ ከ400 በላይ ፕሮጀክቶች መካከል አሸናፊ በመሆን የተገኘ ዕድል ነው፡፡

Scroll to Top