የኃይል ምንጭ ጥገኝነትን መቀነስ!

የኃይል ምንጭ ጥገኝነትን መቀነስ!

ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት በውሃ ኃይል (Hydro-power) ላይ ጥገኛ ሆና ቆይታለች። ይሁንና የኃይል ስብጥሩን ለማስፋት የተለያዩ ሥራዎች በመሰራት ላይ ናቸው፡፡ በቀጣይ ዓመታ ይተገበራሉ ተብለው በዕቅድ ከተያዙት መካከል የንፋስና የፀሐይ ኃይልን በስፋት ማካተቷ የአቅርቦት አስተማማኝነትን (Power Supply Reliability) ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ በመሆኑም የኃይል ምንጭ ጥገኝነት (Over-reliance on Hydropower) መቀነስ የሚኖሩትን አራት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታዎች ቀጥለን እንመለከታለን።

የአየር ንብረት ለውጥንና ድርቅን መቋቋም (Climate Resilience)

የውሃ ኃይል ማመንጫዎች የዝናብ መጠን ሲቀንስ እና የግድቦች ውሃ የመያዝ አቅም ሲቀንስ የማመንጨት አቅማቸው በከፍተኛ መጠን ይቀንሳል። ስለሆነም እንደ ንፋስና ፀሐይ ባሉ ሌሎች ታዳሽ የኃይል ምንጮች ላይ ኢንቨስት ማድረጓ የሚከተሉትን ጥቅሞች ይሰጣል፡፡
በኢትዮጵያ ድርቅ ወይም የበጋ ወቅት በሚሆንበት ጊዜ የውሃ መጠን ቢቀንስም የንፋስ ፍጥነትና የፀሐይ ሙቀት ግን ይጨምራሉ። ይህ አንዱ ሲቀንስ ሌላው እንዲተካ በማድረግ የኃይል መቆራረጥን በመቀነስ አስተማማኝነቱን ይጨምራል፡፡

በቀን የፀሐይና የንፋስ ኃይልን በመጠቀም በግድቦች ውስጥ ያለውን የውሃ ክምችት ደግሞ ለምሽት የኃይል ፍላጎት (Peak hours) ማሟያ በመጠቀም የግድቦችን የውሃ ክምችት ለመቆጠብ ይረዳል።

የኃይል ምንጭ ስብጥርና ስጋትን መቀነስ (Diversification)
አንድ ሀገር በአንድ የኃይል ምንጭ ላይ ብቻ ጥገኛ መሆኑ ለከፍተኛ ስጋት ያጋልጠዋል። የንፋስና የፀሐይ ኃይልን ከሌሎች የኃይል ምንጮች ጋር መጠቀም ይህንን ስጋት የሚቀንሰው በሁለት መንገድ ነው፡፡
በአንድ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ላይ የቴክኒክ ብልሽት ቢከሰት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የንፋስና የፀሐይ ኃይል ማምንጫዎች የኃይል አቅርቦቱ ሙሉ በሙሉ እንዳይቋረጥ እንደ ዋስትና ያገለግላሉ።

የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ለመገንባት ከአምስት ዓመት ያላነሰ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል፡፡ የንፋስና የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር እንካልሆነ ድረስ ከ 1 – 2 ዓመት ባለ ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ወደ ሥራ ስለሚገቡ ለተለዋዋጭ የኃይል ፍላጎት ፈጣን ምላሽ ይሰጣሉ።

ያልተማከለ ስርጭት (Decentralized Grid)
የውሃ ኃይል ማመንጫዎች የሚገነቡት ወንዞች ባሉባቸው ራቅ ያሉ አካባቢዎች በመሆኑ፣ ኃይሉን ረጅም ርቀት ለማጓጓዝ ከፍተኛ ወጪ ይፈልጋል፤ የመነጨ ኃይል ረጅም ርቀት ሲጓጓዝ ደግሞ የኃይል ብክነት ይኖራል።
የፀሐይና የንፋስ ኃይልን የኃይል ፍላጎት ባለባቸው የኢንዱስትሪ መንደሮችና ከተሞች አቅራቢያ መገንባት በመገንባት ከግሪድ ጋር እንድያያዙ አልያም ከግሪድ ጋር ሳይያያዙ እንዲሰሩ ማድረግ ይቻላል። ይህም በማስተላለፊያ መስመሮች ላይ የሚከሰተውን የኃይል ብክነት (Transmission loss) ለመቀነስ ያግዛል፡፡

ለቀጣናዊ የኃይል ሽያጭ የሚኖረው ሚና
ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ኃይል በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት አስተማማኝ ያደርገዋል።
በአንድ የኃይል ምንጭ ላይ የሚኖረውን ጥገኝነት መቀነስ በድርቅ ወቅት ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ሀገር ሽያጭ የሚሆን ኃይል ከተለያዩ ታዳሽ የኃይል ምንጮች ደጋፊ ኃይል በማግኘት ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ማማ ለመሆን የጀመረችውን ጉዞ ያጠናክራል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የኢነርጂ ፖሊሲ ለውጥ “ሁሉንም እንቁላሎች በአንድ ቅርጫት አለማስቀመጥ” የሚለውን ጥበብ የተከተለ ሲሆን፣ ይህም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከወቅታዊ የዝናብ መዛባትና ከኃይል እጥረት ይታደጋል።

Scroll to Top