በባህር ዳር ከተማ የተገነባው የባለ 230 ኪሎ ቮልት ተንቀሳቃሽ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ምዕራብ ሪጅን አስታወቀ።
የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ተሻገር እንደገለፁት በከተማዋ አንድ ባለ 400/230 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ የሚገኝ ቢሆንም እያደገ የመጣውን የነዋሪውን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ጥያቄ የሚመልስ አልነበረም፡፡
ነባሩ የባህር ዳር የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ለከተማዋና አካባቢው ኢንዱስትሪዎች 125 ሜጋ ዋት ኃይል እያቀረበ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ሆኖም ጣቢያው ኃይል የመጫን አቅሙ በመሙላቱ ምክንያት ተጨማሪ ጥያቄዎችን ማስተናገድ የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት አገልግሎት መስጠት የጀመረው ተንቀሳቃሽ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ተጨማሪ 47 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ በማቅረብ በከተማዋ ይስተዋል የነበረውን የኃይል መቆራረጥ እና የቮልቴጅ መዋዠቅ ችግር በጊዜያዊነት ይፈታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው ያብራሩት፡፡
ጣቢያው ባህርዳር ከተማን ጨምሮ ሐሙሲት ከተማ እና በዙሪያው የሚገኙ አካባቢዎችን የኃይል አቅርቦቱ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ተሻገር ገለፃ ጣቢያው 50 ሜጋ ቮልት አምፒር ኃይል የመጫን አቅም ያለው አንድ ትራንስፎርመር እንዲሁም አንድ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ገቢ እና አምስት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች አሉት፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በኩል ከ53 ሜጋ ዋት በላይ የኃይል ፍላጎት ጥያቄ ያቀረቡ ደንበኞች ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙም ነው የጠቀሱት፡፡
ስለሆነም አሁን እየቀረቡ ያሉትን ጥያቄዎችና ወደፊት የሚመጣውን የኤሌክትሪክ ፍላጎት በዘላቂነት ለመመለስ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን መገንባት እንደሚስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

