በምዕራብ አርሲ ዞን እና በአካባቢው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማርካት በሻሸመኔ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ሁለተኛ ዙር የአቅም ማሳደግ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለፁ፡፡
ሥራ አስኪያጁ አቶ ምህረቱ ግዛው እንደገለፁት ጣቢያው ከ1966 ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ መቆጣጠሪያዎችን በዘመናዊ የጂ.አይ.ኤስ ብሬከሮች በመቀየር አስተማማኝና ያልተቆራረጠ ኃይል ለማቅረብ እየተሰራ ነው።


ቀደም ሲል በማከፋፈያ ጣቢያው የነበሩት የ33 እና 15 ኪሎ ቮልት መቆጣጠሪያ ብሬከሮች በዘመናዊ የጂ.አይ.ኤስ ብሬከሮች ተቀይረው አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ሥራ አስኪያጁ አስታውሰዋል፡፡


ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ከዞኑ እንቅስቃሴ፣ ከከተማዋ እና አካባቢው ዕድገት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት ጥያቄዎች በመኖራቸው ምክንያት ለሁለተኛ ጊዜ የሚከናወነው የ15 ኪሎ ቮልት የጂ.አይ.ኤስ መቆጣጠሪያ ብሬከር ግንባታ የሲቪል ሥራ 60 በመቶ መድረሱን ገልፀዋል፡፡
ይህም የጣቢያውን የኦፕሬሽን አቅም ከማዘመኑም ባሻገር ለአካባቢው ህብረተሰብ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ መፍትሔ ለመስጠት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ምህረቱ ገለፃ የማከፋፈያ ጣቢያውን አቅም ይበልጥ ለማሳደግ የሚያስችል ተጨማሪ የኃይል ትራንስፎርመር ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ማከፋፈያ ጣቢያው ካለው 60 ሜጋ ዋት የመጫን አቅም ውስጥ 52 ሜጋ ዋቱ መጫኑንና ከጊዜ ወደ ጊዜ የደንበኞች የኃይል ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል።
የሻሸመኔ ማከፋፈያ ጣቢያ 50 እና 25 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው ሁለት የኃይል ትራንስፎርመሮች፣ አራት ገቢ መስመሮች እንዲሁም አንድ ባለ 132፣ ሦስት ባለ 33 እና ዘጠኝ ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች አሉት፡፡
ማከፋፈያ ጣቢያው ለአዳሚ ቱሉ፣ ለሜጢ፣ ለዋርካ፣ ለወንዶ ገነት፣ ለአርሲ ነገሌ፣ ለኮፈሌ እና ለሻሸመኔ ከተሞች እንዲሁም በዙሪያቸው ለሚገኙ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አቅርቦት እየሰጠ ይገኛል፡፡
