‎ማከፋፈያ ጣቢያው ተጨማሪ የኃይል ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ዝግጁ ነው

‎ማከፋፈያ ጣቢያው ተጨማሪ የኃይል ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ዝግጁ ነው

‎የጅግጅጋ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ተጨማሪ የኃይል ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።

‎ሥራ አስኪያጁ አቶ ደምለው እሸቱ እንደገለጹት ‎በማከፋፈያ ጣቢያው ላይ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በተከናወኑ የአቅም ማሳደግና የማዘመን ሥራዎች አሁን ላይ የጅጅጋ ከተማና አካባቢው አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል እያገኙ ነው።

ጣቢያው እስከ 60 ሜጋ ዋት ኃይል የማቅረብ አቅም ቢኖረውም በአሁኑ ወቅት ለደንበኞች እየቀረበ ያለው የኃይል መጠን 30 ሜጋ ዋት ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ደምለው ገለጻ በከተማዋና አካባቢው በመገንባት ላይ ለሚገኙ ፋብሪካዎችና በቀጣይ ለሚመጡ ኢንቨስትመንቶች አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ጣቢያው ‎‎ዝግጁ ቢሆንም ከድሬዳዋ – ሐረር ያለው የማስተላለፊያ መስመር የመጫን አቅም እየተዳከመ መጥቷል፡፡

‎ይህም በጣቢያው የኦፕሬሽን ሥራዎች ላይ ጫና እየፈጠረ በመሆኑ በመስመሩ ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ከሐረር ቁጥር 3 ማከፋፈያ ጣቢያ ባለ 132 ኪሎ ቮልት አንድ ገቢ እንዲሁም አንድ ባለ 132 ኪሎ ቮልት፣ አራት ባለ 33 እና አራት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች አሉት።

‎ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2018 በጀት ዓመት ያለፉት ዘጠኝ ወራት የኦፕሬሽን ሥራውን የሚያቀላጥፉ የክትትል፣ የፍተሻና የቁጥጥር ሥራዎች እንዲሁም ምቹ የሥራ ከባቢ ለመፍጠር የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውንም ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል።

‎በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራትም የጣቢያውን ዝግጀነትና አስተማማኝነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

‎የጅጅጋ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ለጅጅጋና አካባቢው አስተማማኝ ኃይል እያቀረበ ይገኛል።

Scroll to Top