የኃይል ማከፋፊያ ጣቢያው የማስፋፊያ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

የኃይል ማከፋፊያ ጣቢያው የማስፋፊያ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

የኃይል ማከፋፊያ ጣቢያው የማስፋፊያ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ የቦሌ ለሚ ባለ 230/33/15 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ግንባታ ሥራ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማዕከላዊ ሁለት ሪጅን የማከፋፈያ  ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የማከፋፈያ ጣቢያዎች ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ተስፋዬ እንዳስታወቁት በማከፋፈያ ጣቢያው የማስፋፊያ ግንባታ የተከናወነው ጣቢያው ኃይል የመጫን አቅሙ በመቀነሱ ሳይሆን በ15 ኪሎ ቮልት ተጨማሪ ኤሌክትሪክ ለማቅረብ በመታሰቡ ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአካባቢው የ15 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር መጨመር ለማስፋፊያ ግንባታው ዋና ምክንያት እንደሆነ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ዮሐንስ ገለፃ የማስፋፊያ ሥራው የተለያዩ የሲቪልና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ግንባታዎችን ጨምሮ አንድ ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያለው ትራንፎርመር የማስቀመጥ፣ የኃይል መቆጣጠሪያ ቤት ግንባታ፣ የጂ.አይ.ኤስ ስዊችጊር ገጠማና በ230 ኪሎ ቮልት በኩል የቤይ ዕቃዎችን የመትከል እንዲሁም የፍተሻና የሙከራ ሥራዎችን ያጠቃልላል።

የቦሌ ለሚ የማከፋፈያ ጣቢያ በተደረገለት የማስፋፊያ ግንባታ በአሁኑ ወቅት ስድስት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች እንደተገነቡለት የገለፁት ሥራ አስኪያጁ ይህም ለቦሌ አራብሳ፣ በሻሌና አካባቢው አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ዝግጁ የተደረጉት አዳዲሶቹ ወጪ መስመሮች ኃይል መስጠት የሚጀምሩት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በኩል የማሰራጫ መስመሮች ከተዘረጉ በኋላ በመሆኑ ለአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና ለዲስትሪክቱ የማሳወቅ ሥራ መሰራቱን አስታውቀዋል፡፡

የማስፋፊያ ግንባታው በሪጅኑ አቅም መከናወኑን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ ይህም አዳዲስ መሐንዲሶች እና የቴክኒክ ባለሙያዎች የልምድና የዕውቀት ሽግግር እንዲያገኙ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን አብራርተዋል።

የማስፋፊያ ግንባታው በሪጅኑ አቅም በመከናወኑ ተቋሙን ከተጨማሪ ወጪ ማዳን እንዳስቻለም ነው አቶ ዮሐንስ የገለፁት።

የማስፋፊያ ሥራው በሪጅኑ አቅም እንዲከናወን የተቋሙ የሥራ አመራር እና የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ ለሰጡት ዕድልና ኃላፊነት እንዲሁም በሥራው ላይ ለተሳተፉ ባለሙያዎች ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

የቦሌ ለሚ የማከፋፈያ ጣቢያ ካሉት 14 ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች መካከል ለኢንዱስትሪዎችና ለከፍተኛ የኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች ኤሌክትሪክ እያቀረቡ የሚገኙት ዘጠኙ ብቻ ናቸው።

ማከፋፈያ ጣቢያው ከ240 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል የመጫን አቅም ያላቸው አንድ ባለ 50 እና  ሁለት ባለ 125 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሮች አሉት።

በ15 ሚሊየን ብር በጀት የተከናወነውን የቦሌ ለሚ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ግንባታ ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት ጊዜ ወስዷል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top