የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን የመቆጣጠሪያ ደህንነት ሥርዓት ለማዘመን እና ለማሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ አስታወቀ።
በዘርፉ የዲጂታላይዜሽን እና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት መምሪያ የምስራቅ አንድ ሪጅን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ጠይብ መሐመድ እንደገለፁት የመቆጣጠሪያ ደህንነት ሥርዓት የማዘመን እና አቅም የማሳደግ ሥራው በተመረጡ 69 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል።
የጣቢያዎችን እና ማስተላለፊያ መስመሮችን የመቆጣጠሪያ ደህንነት የማዘመን እና የማሻሻል ሥራው በማዕከላዊ አንድ፣ ማዕከላዊ ሦስት እና ምስራቅ አንድ እንዲሁም ደቡብ አንድ ሪጅን ሥር በሚገኙ 15 የኃይል ማከፋፊያዎች ላይ መጀመሩንም ነው የተናገሩት።
በአሁኑ ወቅት የአምስት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን የመቆጣጠሪያ መሳሪያዎች የማዘመን እና አቅም የማሳደግ ሥራ ተጠናቆ ሥራ መጀመራቸውንም ነው የገለፁት።
እንደ አቶ ጠይብ ገለፃ ፕሮጀክቱ በዋናነት በማከፋፈያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ትራስፎርመሮችን እና የመቆጣጠሪያ መሳሪያዎችን ደህንነት በማዘመን ለደንበኞች አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ማስቻል ነው።
በተቋሙ የኢንጅነሪንግ ዘርፍ የኮንትራት እና ሱፐርቪዥን መምሪያ የምስራቅ አንድ ሪጅን አስተባባሪ አቶ ክብሮም በርሔ በበኩላቸው የሥራ ክፍሉ የፕሮጀክቱን እንቅስቃሴ የመቆጣጠር እና በኮንትራቱ መሰረት እንዲጠናቀቅ የማድረግ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ደህንነት ለረጅም ዓመታት ሲቆጣጠሩ የቆዩ፣ የተበላሹ እና ውስንነት ያለባቸው የሪሌይ ዕቃዎችን በአዲስና ዘመናዊ መሳሪያዎች ለመቀየር ያለመ እንደሆነም ነው የገለፁት።
እንደ አቶ ክብሮም ገለፃ በጣቢያዎቹ የሚገጠሙት ዘመናዊ የመቆጣጠሪያ መሳሪያዎች የማከፋፈያ ጣቢያዎቹን ደህንነት የማስጠበቅ ሥራ ወጥነት ባለው መልኩ በአንድ ሪሌይ ብቻ የማከናወን አቅም የሚፈጥሩ ናቸው።
የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን የመቆጣጠሪያ ሥርዓት የማዘመንና አቅም የማሳደግ ሥራውን የቻይናው ሲ.ዋይ.ጂ ሱርሚ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ እያከናወነ ሲሆን የተቋሙ የኮንትራት እና ሱፐርቪዥን መምሪያ ደግሞ በአማካሪነት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ፕሮጀክቱን በ18 ወራት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ከ4.6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ በጀት የተያዘ ሲሆን የፋይናንስ ወጪውም ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸፈን ነው።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



