የኃይል ማመንጫ ግድቡን ደህንነት ለመጠበቅ እየተሰራ ነው

የኃይል ማመንጫ ግድቡን ደህንነት ለመጠበቅ እየተሰራ ነው

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የግልገል ጊቤ አንድ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጣቢያው አስታወቀ።

የጣቢያው የጥገናና የዳም ሞኒተሪንግ ሥራ ክፍል መሪ አቶ ሀብታሙ ጌቱ እንደተናገሩት የዕይታ ፍተሻ እና የግድብ ደህንነት መከታተያ መሣሪያዎችን በመጠቀም የኃይል ማመንጫውን ግድብ ደህንነት የማረጋገጥ ሥራ እየተሰራ ነው፡፡

የግድብ ደህንነት ክትትልና ቁጥጥር ሥራው በውሃ መግቢያው (ኢንቴክ)፣ በውሃ ማስተንፈሻ (Spillways) እና በግድቡ የተለያዩ ክፍሎች ላይ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

የግድቡ ስርገትን (Dam settlement) በተመለከተ በዲዛይን ወቅት በተቆፈሩና እስከ 38 ነጥብ 2 ሜትር ጥልቀት ባላቸው አምስት ጉድጓዶች ውስጥ በተቀመጡ ቀለበቶች አማካኝነት ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በተጨማሪም 1 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር በሚረዝመው በግድቡ ሥር ባለ የመሬት ውስጥ ዋሻ የታችኛው ወለል የውሃ ፍሳሽ መጠን መቆጣጠሪያዎች አማካኝነት የቁጥጥር ሥራ ይሰራል።

ይህም የግድቡን ደህንነት ስጋት ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ያልተጠበቁ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ክስተቶችን በመከላከል እና አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ በወቅቱ በመውሰድ ደህንነቱን ለመጠበቅም ያግዛል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በግድቡ የሚከናወነው የክትትልና ቁጥጥር ሥራ የግድቡን ደህንነት በመጠበቅ የኃይል ማመንጫ ጣቢያው የሚጠበቅበትን ኃይል በአግባቡ እንዲያመርት ከማድረግ ባሻገር ከግድቡ በታች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከድንገተኛ ጎርፍ ለመከላከል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የግድብ ክትትልና ቁጥጥር ሥራው በግድቡ ላይ በየሳምንቱና በየወሩ ፍተሻ በማካሄድ የሚከናወን መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ደህንነት ለመጠበቅ በዲዛይን፣ በግንባታ ሂደት፣ ግድቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ውሃ መያዝ ሲጀምር እንዲሁም በአገልግሎት ጊዜ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎችን ያከናውናል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top