የደብረ ብርሃን ቁጥር አንድ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያን አቅም ለማሳደግና የማሻሻያ ሥራዎችን ለማከናወን እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ።
ሥራ አስኪያጁ አቶ አደፍርስ በለጠ እንደገለፁት ከ1970ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ በሚገኘው የማከፋፈያ ጣቢያ ላይ ሊከናወኑ የታቀዱት የአቅም ማሳደግ ሥራዎች ለደብረ ብርሃን ከተማና ለአካባቢው የኃይል ፍላጎት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ ናቸው፡፡
የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ለአዳዲስ ደንበኞች ተጨማሪ ኃይል ለማቅረብ እንዲችል በ33 ኪሎ ቮልት መስመሮች ላይ የአቅም ማሳደግና ማሻሻያ ሥራዎች መከናወናቸውን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም በ15 ኪሎ ቮልት መስመሮች ላይ የዘመናዊ ስዊች ጊር ገጠማ ሥራዎችን ለማከናወን እንቅስቃሴ መጀመሩን የጠቀሱት አቶ አደፍርስ ይህም የጣቢያውን የኦፕሬሽን ሥራዎች ለማዘመን እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ በመቆየቱ ምክንያት በመቆጣጠሪያ ክፍሉ ውስጥ የነበሩት በአየር የሚሰሩት ስዊች ጊሮች በተደጋጋሚ ለብልሽት ስለሚዳረጉ ከፍተኛ የኃይል መቆራረጥ ያጋጥም ነበር።
መቆጣጠሪያው በዘመናዊ የጂ.አይ.ኤስ ስዊች ጊር መቀየሩ የኃይል መቆራረጥንና በጥገና ሥራዎች ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በመቅረፍ የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎችን በቀላሉ ለማከናወን እንደሚረዳም ነው የጠቆሙት።
ማከፋፈያ ጣቢያው 31 ሜጋ ዋት ኃይል የመጫን አቅም ያለው አንድ ባለ 25 እና አንድ ባለ 16 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሮች እንዳሉትም ነው የገለፁት።
የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው አንድ ባለ 132፣ አምስት ባለ 33 እና አራት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች አሉት።
ጣቢያው ከለገጣፎ ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል ተቀብሎ በአስሩ የ132፣ 33 እና 15 ኪሎ ቮልት መስመሮች ለሽዋሮቢት፣ ደብረ ብርሃን ፣ መንዲዳ፣ አንኮበር፣ ሰላድንጋይ እንዲሁም አልዩ አምባ ከተሞች ኃይል እያቀረበ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ በጣቢያው የሚገኘው ባለ 16 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመር በ33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመር ለዳሽን ቢራ ፋብሪካ ኃይል እያቀረበ እንደሚገኝም ነው የጠቆሙት።
በአሁኑ ወቅት በኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ውስጥ በሥራ ላይ የሚገኘው ባለ 25 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመር ተጨማሪ ኃይል የመሸከም አቅም እንደሌለው የጠቆሙት አቶ አደፍርስ ኃይል የመጫን አቅማቸው ከፍ ባሉ ትራንስፎርመሮች እንዲቀየሩ ጥያቄ መቅረቡንም ነው የተናገሩት።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



