በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቢሾፍቱ ቁጥር 3 ባለ 400 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ ተጨማሪ ደንበኞችን የማስተናገድ አቅም እንዳለው የጣቢያው ተወካይ ኃላፊ ገለጹ፡፡
ኃላፊው አቶ ሀብታሙ ከበደ እንደገለጹት ማከፋፈያ ጣቢያው በ 400/230 ኪሎ ቮልት ሁለት አውቶ ትራንስፎርመሮች 1 ሺ 200 ሜጋ ቮልት አምፔር የመጫን አቅም ቢኖረውም አሁን ላይ እየሰጠ የሚገኘው ከ15 ነጥብ 6 በመቶ ያልበለጠ ነው።
ቢሾፍቱ የኢንዱስትሪ መናኸሪያ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ በአሁኑ ወቅት በርካታ ኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎች በመገንባት ላይ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ኃብታሙ ማከፋፈያ ጣቢያው በግንባታ ላይ ለሚገኙና በቀጣይ የሚመጡ የኃይል ጥያቄዎችን ለመመለስ ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የኃይል አቅርቦት ችግር እንዳያጋጥም በማከፋፈያ ጣቢያው ላይ የማሻሻያና የማዘመን ሥራዎች መከናወናቸውንም ተወካይ ኃላፊዉ ጠቁመዋል፡
ግንባታው በተጠናቀቀበት ወቅት 50 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያላቸው 230/15 ኪሎ ቮልት ሁለት ፓወር ትራንስፎርመር ብቻ የነበረ ሲሆን በአካባቢው በባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመር ከፍተኛ ፍላጎት በመኖሩ ምክንያት ተጨማሪ 50 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያላቸው 230/33 ኪሎ ቮልት ሁለት ፓወር ትራንስፎርመሮች ማስፋፈያ ተደርጓል፡፡
እንደ አቶ ሀብታሙ ገለፃ ማከፋፈያ ጣቢያው ሁለት ባለ 400 ኪሎ ቮልት ከገላን ማከፋፈያ ጣቢያ ገቢ መስመር ያለው ሲሆን በ230 ኪሎ ቮልት ለዱከም ቁጥር-2 በሁለት መስመሮች እንዲሁም ለሞጆ ማከፋፈያ ጣቢያዎች በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡


ጣቢያው አስር ባለ15 ኪሎ ቮልት እና አስር ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች እንዳሉትም አመላክተዋል፡፡
በማከፋፈያ ጣቢያው ያሉት ብሬከሮች ጂ አይ ኤስ በመሆናቸው የኃይል መቆራረጥን በመቀነስ በኩል ሚናቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በትራንስፎርመሮች ውስጣዊ ችግር ምክንያት የእሳት አደጋ ቢከሰት አደጋውን ለመከላከል የሚረዳ ጨምሮ ሌሎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የቢሾፍቱ ቁጥር 3 ባለ 400 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ ከመስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቀላቀል ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ያግኙ
ፌስቡክ↠ https://www.facebook.com/Ethioelectric
ቴሌግራም↠ https://t.me/EEPCommuication
ትዊተር ↠ https://twitter.com/EEPethiopia
ዩትዩብ ቻናል↠ https://www.youtube.com/@ethiopowermedia
ቲክቶክ አካውንት↠https://tiktok.com/@ethio_power
ድረ – ገፃችንንም ይጎብኙ www.eep.com.et
ታህሳስ 16 ቀን 2017 ዓ.ም


