የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም ለማሳደግና ለማዘመን እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡
በተቋሙ የማከፋፈያ ጣቢያዎች እና ማስተላለፊያ መስመሮች ኦፕሬሽን አገልግሎት መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ወ/ማርያም እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ በ24 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የ15 አና 33 ኪሎ ቮልት ስዊችጊሮችን ለማዘመን ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
በበጀት ዓመቱ ያለፉት ወራት በሆርማት፣ አዋሽ 7 ኪሎ፣ ወልቂጤ፣ ኮምቦልቻ፣ ወላይታ ሶዶ አንድ እና ዓለም ከተማ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የማዘመን ሥራው ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን አብራርተዋል።
ተጨማሪ ደንበኞችን ማስተናገድ የማይችሉ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን በመለየት የአቅም ማሳደግ ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ዳይሬክተሩ አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅትም በሱሉልታ፣ ኮምቦልቻ ሁለት፣ ለገጣፎ፣ ጅማ እንዲሁም በሚዛን እና ባሌ ሮቤ ተንቀሳቃሽ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ከ50 እስከ 250 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ያላቸው ትራንስፎርመሮች እየተተከሉ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡
የአቅም ማሳደግ ያስፈልጋቸዋል ተብለው በተለዩ ሌሎች የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ተመሳሳይ ሥራዎችን ለማከናወን የትራንስፎርመር ግዥ በሂደት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ለጥገና አገልግሎት የሚያገለግሉ መለዋወጫ ዕቃዎች፣ የ15 እና 33 ኪሎ ቮልት ብሬከሮች፣ ባትሪዎች እንዲሁም የሆለታ እና ደዴሳ ማከፋፈያ ጣቢያዎችን የቮልቴጅ መዋዥቅ ለማስተካከል የሚረዳ የSVC መለዋወጫ ዕቃዎች እና የከፍተኛ ቮልቴጅ መለዋወጫ ዕቃዎች በተቋሙ መጋዘን መኖራቸውን ገልፃዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የዕቃ ማንሻ ክሬኖችን ጨምሮ ለኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች የመለዋወጫ ዕቃዎችንና መሣሪያዎችን ለማሟላት በግዥ ሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡
በማከፋፈያ ጣቢያዎች ያለአግባብ የተቀመጡ ንብረቶችን በሥርዓት ለማስቀመጥ የሚያስችሉ 17 የዕቃ ግምጃ ቤቶች በስምንት ሪጅኖች ላይ እየተሰሩ ሲሆን ከነዚህም መካከል የከምሴ፤ ኮምቦልቻ ሁለት፤ አንፎ ሜዳ፤ ጅጅጋ እና የሐዋሳ ሁለት ማከፋፈያ ጣቢያ የዕቃ ግምጃ ቤቶች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የአደጋ ጊዜ የከፍተኛ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎችን (emergency restoration tower) ወደ ሥራ ለማስገባት የባለሙያዎችን አቅም የሚያሳድግ የተግባር ላይ ሥልጠና በመስጠት አሁን ላይ ሥራው ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ለተቋሙ ፈተና የሆነውን የከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ የብረት ምሰሶ ስርቆት ለመከላከልና በግሪድ ሥርዓቱ ላይ የሲስተም መረበሽ እንዳያጋጥም ችግሩ በስፋት የሚስተዋልባቸው ቦታዎችን በመለየት የፍተሻ ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ተቋሙ በ13 ሪጅኖች 145 ማከፋፈያ ጣቢያዎችን ያስተዳድራል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”