“የኃይል መሰረተ ልማት ደህንነትን ማስጠበቅ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው” ‎ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ

“የኃይል መሰረተ ልማት ደህንነትን ማስጠበቅ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው” ‎ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ

የኃይል መሰረተ ልማት ደህንነትን ማስጠበቅ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ በመሆኑ በትኩረት መስራት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ገለፁ፡፡

‎በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ለተመለመሉ የኃይል መሰረተ ልማት ጥበቃ አባላት ሲሰጥ የቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና የተቋሙን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጨምሮ የመከላከያ ሚኒስቴር እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተጠናቋል፡፡

በሥልጠናው ማጠናቀቂያው ላይ ለሠልጣኝ አባላቱ የሥራ መመሪያ የሰጡት ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርስ ጉዳት የኦፕሬሽን ሥራዎችን በማስተጓጎል በሀገር ሁለንተናዊ ዕድገትና ሠላም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ተናግረዋል፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ሆነው ከ30 ዓመት በላይ ሀገርን ያገለገሉት ሠልጣኝ አባላቱ ወደ ተቋሙ መምጣት የኃይል መሰረተ ልማትን ደህንነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት ተጨማሪ ጉልበት የሚሰጥ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ከፍተኛ የኃይል መሰረተ ልማት ሥርቆት የሚስተዋሉባቸው አካባቢዎች በዘርፍ ተለይተው የከፍተኛ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎችንና ማስተላለፊያ መስመሮች ጥበቃ መጀመሩን ጠቁመዋል።

የኃይል መሰረተ ልማት ደህንነትን ማስጠበቅ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ በመሆኑ ሠልጣኝ አባላቱ በሕብረተሰቡና በተቋሙ መካከል ድልድይ ሆነው በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

ለሥራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ ለማሟላት ጥረት እንደሚደረግ የተናገሩት ኢንጂነር አሸብር ተቋሙ በኃይል መሰረተ ልማት ደህንነት ጥበቃ ላይ ለውጥ ለማምጣት የመከላከያ ሚኒስቴር እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የመከላከያ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው ሠልጣኝ አባላቱ በተመደቡባቸው ሪጅኖች በኃይል መሰረተ ልማት ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ስጋቶችን በመለየት፣ ትክክለኛ መረጃ በማሰባሰብና ሕብረተሰቡንና መንግስታዊ መዋቅሩን በማሳተፍ በዕቅድ ላይ ተመስርቶ የቅድመ መከላከል ሥራዎችን ማከናወን ይገባል ብለዋል።

የኃይል መሰረተ ልማት ደህንነትን ማስጠበቅ የተቋማቱ ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነት መሆኑን የጠቆሙት የሥራ ኃላፊዎቹ በቀጣይም በመረጃ ልውውጥ፣ በአቅም ግንባታና መሰል ሥራዎች ከተቋሙ ጋር በትብብር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

በተቋሙ፣ በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና በመከላከያ ሚኒስቴር ሲሰጥ የቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በተቋሙ ርዕይና ተልዕኮ፣ አሰራርና አደረጃጀት እና በቁልፍ ተቋማት መሰረተ ልማት ጥበቃ እንዲሁም በደህንነት ስጋት የመረጃ አሰባሰብ ዘዴ ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ነበር።
                                                                                                                                                                                                                                                                                   ? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top