የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የከርሰምድር እንፋሎት ኃይልን በአግባቡ ለመጠቀም በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት እንደሚገባ በተቋሙ የጂኦተርማል ልማት ቢሮ ገለፀ፡፡
ተቋሙ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በተከፈተው 4ኛው ዓመታዊ የማዕድን እና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ (MINTEX Ethiopia 2025) ላይ በከርሰምድር እንፋሎት የኃይል ልማት ላይ እያከናወናቸው የሚገኙ ሥራዎችን እና የዘርፉን የወደፊት ዕቅዶች የሚያሳዩ መረጃዎችን ለዕይታ አቅርቧል።
የኤግዚቢሽኑ አስጎብኚ የጂኦተርማል ከፍተኛ ባለሙያው አቶ ሰለሞን ከበደ እንደተናገሩት ተቋሙ የኃይል ስብጥርን ለማሳደግና የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ በከርሰምድር እንፋሎት ሀብት በተፈጥሮ የታደለች መሆኗን የጠቀሱት ባለሙያው ይሁን እንጂ ዘርፉ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እና የሰለጠነ የሰው ኃይል የሚፈልግ በመሆኑ እምቅ ሀብቱን በአግባቡ መጠቀም እንዳልተቻለ ገልፀዋል፡፡
በዚህም ተቋሙ የከርሰምድር እንፋሎት ኃይል ግንባታ ዘርፍን ለማሳደግ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ ጠንክሮ መስራት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል፡፡
እንደ አቶ ሰለሞን ገለፃ ኤክስፖው የከርሰምድር እንፋሎት በኃይል ልማት ዘርፉ ላይ ያለውን ድርሻ እና ፋይዳ ለህብረተሰቡ ለማስተዋወቅ ይረዳል፡፡
በማዕድን ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት እና በማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በጋራ የተዘጋጀው 4ኛው ዓመታዊ የማዕድን እና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ እስከ ህዳር 7 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለጎብኝዎች ክፍት መደረጉም ታውቋል።
ኤክስፖውን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻን ጨምሮ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ጎብኝተውታል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”






