የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል መሰረተ ልማት ጥበቃ አባላት የተቋሙን መሰረተ ልማቶች ከስርቆት ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መስራት እንደሚጠበቅባቸው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አሳሰበ፡፡
አገልግሎቱ በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ለተመለመሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል መሰረተ ልማት ጥበቃ አባላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡
ሥልጠናው በቁልፍ ተቋማት መሰረተ ልማት ጥበቃ ዙሪያ ያተኮረ ሲሆን አባላቱ ስለቁልፍ ተቋማት ምንነት፣ ሀገራዊ ፋይዳ፣ ደህንነት እና ስጋቶች በተመለከተ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ የኃይል መሰረተ ልማቶችን ደህንነት እንዲያስጠብቁ ለማስቻል ያለመ ነው፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በአዋጅ ቁጥር 1278/2014 መሰረት በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ቁልፍ የመሰረተ ልማቶችን ደህንነት ደረጃ(standard) የማውጣት እንዲሁም በደህንነት ጥበቃ ላይ ለሚሰማሩ ባለሙያዎች ሥልጠና የመስጠት ተልዕኮ እንዳለውም ተገልጿል፡፡
በዚህም ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ቁልፍ የሆነውን የኃይል መሰረተ ልማት ጥበቃ ደህንነት ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በየ24 ሰዓቱ መረጃ በመለዋወጥ እና ጥናቶችን በማድረግ በትብብር እየሰራ መሆኑም ተብራርቷል፡፡
በቁል መሰረተ ልማቶች ጥበቃ ዙሪያ እየተሰጠ ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና የሁለቱ ተቋማት ትብብር ማሳያ መሆኑንም ነው የተጠቆመው፡፡
ሠልጣኝ አባላቱ በተመደቡባቸው ሪጅኖች ከሥልጠናው ያገኟቸውን ዕውቀቶች በመተግበር፣ መረጃዎችን በማደራጀት፣ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን አስቀድሞ በመለየት እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የኃይል መሰረተ ልማት ደህንነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ተጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም አባላቱ ነባራዊ ሁኔታዎችን እና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ከግምት በማስገባት የተቋሙን መሰረተ ልማቶች ከአደጋ የመከላከልና ፈጣን ምላሽ የመስጠት ተግባራትን ማከናወን እንዳለባቸው ተብራርቷል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በቀጣይም የ24 ሰዓት የመረጃ ልውውጡን በማጠናከር እና በኃይል መሰረተ ልማት ደህንነት ላይ ያሉ ስጋቶችን በየጊዜው በመተንተን ቀጣይነት ያለው የአቅም ግንባታ ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አረጋግጧል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


