በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቁጥር ተከትሎ የተሽከርካሪዎች የኃይል ፍላጎት በ2017 ዓ.ም ከነበረበት 370 ጊጋ ዋት ሰዓት በ2022 ዓ.ም ወደ 2.7 ቴራ ዋት ሰዓት እንደሚያድግ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያስጠናው አንድ ጥናት አመለከተ፡፡
ተቋሙ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ተፅዕኖ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የግሪድ ሲስተም ላይ በሚል ርዕስ ያስጠናውን ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡
ጥናቱ የተሸከርካሪዎቹ የኃይል ፍላጎት፣ መሰረተ ልማቶች ላይ ያላቸው ተጽዕኖ፣ የቮልቴጅ መረጋጋትን ከማስተካከል አኳያ እና እነዚህን ተፅኖችን ለመቋቋም የሚያስችሉ የመፍትሄ ሀሳቦችን በዝርዝር ዳሷል፡፡
የኢፊዲሪ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር ያዘጋጀውን ስትራቴጂክ እቅድ መሰረት በማድረግ የተከናወነው ጥናቱ ከ2017-2022 ዓ.ም ያለውን ጊዜ የኃይል አጠቃቀም አዝማሚያ የሚዳስስ እንደሆነ የጥናቱ ቡድን መሪ ኢንጅነር ሀብታሙ አበበ ገልፀዋል፡፡
እንደ ኢንጅነሩ ገለፃ በዚህ ጥናት የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች በዓይነት እና በፍጆታ መጠናቸውን መለየታቸውን አመልክተው ባሶች በኃይል ፍጆታ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ ገልፀዋል፡፡
ተቋሙ ይህን የኃይል ፍላጎት ለመመለስ የሚያስችል አቅም መገንባቱን የገለፁት ኢንጂነር ሀብታሙ የብሔራዊ ኃይል ቋቱ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ከወዲሁ መስራት እንደሚገባዉ ጠቁመዋል፡፡
ጥናቱ በተቋሙ ባለሙያዎች የተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የኢትዮ-ፓዎር አካዳሚ ዳይሬክተር ዶ/ር ወንድወሰን ካሳ ውስጣዊ ትብብርን በማጠናር የተቋሙን ያልተዳሰሱ ገፅታዎች በጥናት ማስተዋወቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”




