በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከሱሉልታ – ደብረ ማርቆስ በተዘረጋው ባለ 400 ኪሎ ቮልት ጥምር መስመር ላይ ስርቆት የፈጸሙ ሦሥት ግለሰቦች በእስራት መቀጣታቸውን የማእከላዊ አንድ ሪጅን የማስተላለፊያ መስመር እና ኦፕቲካል ፋይበር ቢሮ ገለጸ፡፡
የቢሮው ሥራ አስኪያጅ አቶ በፍቃዱ በቀለ እንዳስታወቁት ስርቆት ሚያዚያ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ከጠዋቱ 3፡00 በሰሜን ሸዋ ዞን በሱሉልታ ወረዳ ልዩ ስሙ ወረ-ኤርሶ ኮሶበር በተባለ ቦታ ተፈጽሟል፡፡
አቶ ቀነኒሳ በቀለ፣ አቶ አዳነ ጥሩነህ እና አቶ አዳነ አሸብር የተባሉ ግለሰቦች የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ብረቶቹን ሰርቀው በማዳበሪያ ይዘው ሲሄዱ በአካባቢው በጥበቃ ስራ ላይ በተሰማሩ የሚሊሻ አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡
ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግንቦት 12 ቀን 2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት እያንዳንዳቸው በሁለት ዓመት እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ማስተላለፉን አቶ በፍቃዱ ተናግረዋል፡፡
በአጥፊዎቹ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የሱሉልታ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት እና የአካባቢው ሚሊሻዎች ላደረጉት አስተዋጻኦ ሥራ አስኪያጁ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

