የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሸገር ከተማ አስተዳደር ከይዞታ ማረጋገጫ፣ ከመሰረተ ልማት ሥርቆትና ከካሳ ክፍያ ጋር የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲፈቱለት የከተማ አስተዳደሩን ጠየቀ፡፡
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ከሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) እና ከሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ ኃላፊዎች እንደገለፁት በከተማ አስተዳደሩ ክልል የሚገኙ የማከፋፈያ ጣቢያዎች ይዞታዎች ከፍተኛ የመሬት ግብር ክፍያ ቀርቦባቸዋል፤ አንዳንዶቹም ግብር ከተከፈለባቸው በኋላ ዳግመኛ ግብር ተጠይቆባቸዋል፡፡
ለግሪዱ ስጋት የሚሆኑና ለተደጋጋሚ የኃይል መቋረጥ ምክንያት የሆኑ ስርቆቶች እየተፈፀሙ በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ የተሰረቁ የኃይል ተሸካሚ ብረታ ብረቶችን በመቆጣጠርና በዘራፊዎች ላይ አስተማሪና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለዓመታት ያልተጠናቀቁ የይዞታ ማረጋገጫ ጉዳዮች እልባት እንዲያገኙ ከተማ አስተዳደሩ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም ቋሚ የግንኙነት መድረኮች በመፍጠር ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ ፍላጎት እንዳለው ተቋሙ አስታውቋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ ከተማ አስተዳደሩ ፈጣንና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት ከያዘው ዕሴት ጋር የሚጋጩ ጉዳዮችን በመለየት እንዲስተካከሉ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ጉዳይ በተለየ ሁኔታ እንደሚመለከት የገለፁት ከንቲባው የተጠቀሱትን ችግሮች በፍጥነት ለመፍታት ኮሚቴ እንደሚቋቋም አረጋግጠዋል፡፡
ከስርቆት ጋር የተነሱትን ጉዳዮችን ይዞ ወደ ወረዳዎች በመውረድ እና ህብረተሰቡን በማሳተፍ ለውጥ ለማምጣት በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በቀጣይ ሊሰራቸው ላሰባቸው የስማርት ከተማና ግዙፍ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልገውን ኃይል ተቋሙ ታሳቢ አድርጎ እንዲሰራም ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በበኩላቸው ተቋሙ ኃይል ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ ዕቅድ መንደፉን ገልፀዋል፡፡
ተቋሙ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በሚሰራቸው ሥራዎች የህብረተሰቡን የኃይል አቅርቦት ጥያቄ እየፈታ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
የሀገሪቱ ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀመው መዲናችን አዲስ አበባና በዙሪያው ያሉት ከተሞች በመሆናቸው መሰረተ ልማቱን በትኩረት መጠበቅ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የሚያጋጥመውን የኃይል መቆራረጥ ችግር ጣት በመጠቋቆም ሳይሆን ተቀራርቦ በመስራት ለመፍታት ተቋሙ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
ኃላፊዎቹ የተጀመረው ግንኙነት በፍጥነት ወደ መሬት እንዲወርድ የጋራ ኮሚቴዎች እንዲዋቀሩና አሰራሩን ህጋዊ ለማድረግ የመግባቢያ ስምምነት እንዲዘጋጅ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡





