ተቋሙ የማማከር ሥራዎችን ከሚያከናውን ኩባንያ ጋር ሥምምነት ተፈራረመ

ተቋሙ የማማከር ሥራዎችን ከሚያከናውን ኩባንያ ጋር ሥምምነት ተፈራረመ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዳር አል ሃንዳሳህ ሼር እና ፓርትነር (Dar Al Handasah Shair and Partners) ከተባለ ኩባንያ ጋር የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የማማከር ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል ሥምምነት በስካይ ላይት ሆቴል ማካሔዱን አስታወቀ።

ሥምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እና የዳር አል ሃንዳሳህ ሼር እና ፓርትነር ኩባንያ (Dar Al Handasah Shair and Partners) የኦፕሬሽን ዳይሬክተር ሚስተር ጣሪቅ አል-ቃኒ ተፈራርመዋል፡፡

ሥምምነቱ ዳር አል ሃንዳሳህ ሼር እና ፓርትነር ኩባንያ ከተቋሙ የኢንጅነሪንግ የሥራ ዘርፍ ጋር በአጋርነት የማማከር ሥራዎችን እንዲያከናውን የሚያስችል ነው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት ሥምምነቱ የተቋሙ የኢንጅነሪንግ ዘርፍ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የማማከር ሥራዎችን መስራት የሚያስችለውን ልምድና ተሞክሮ እንዲያገኝ ዕድል ይፈጥራል።

ኩባንያው የተቋሙን ዋና መስሪያ ቤት ህንፃ ዲዛይን እና የቁጥጥር ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ከተቋሙ የኢንጅነሪንግ የሥራ ዘርፍ ጋር በአጋርነት ለመስራት በአዲስ ምዕራፍ መምጣቱንም ተናግረዋል፡

የዳር አል ሃንዳሳህ ሼር እና ፓርትነር ኩባንያ የኦፕሬሽን ዳይሬክተር ሚስተር ጣሪቅ አል-ቃኒ በበኩላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ልምድና ዕውቀት ያለው የማማከር አገልግሎት መስጠት የሚችል ኩባንያ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኢነርጂ ዘርፍ በምስራቅ አፍሪካ ግዙፉ ኩባንያ መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሩ የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ከተቋሙ የኢንጅነሪንግ የሥራ ዘርፍ ጋር በአጋርነት የማማከር አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸውን ሥምምነት ማድረጋቸው ትልቅ ዕድል መሆኑንም ጨምረው ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ኩባንያቸው የበኩሉን ሚና እንደሚወጣም ነው የተናገሩት።

ሥምምነቱ የፕሮጀክቱን ቀሪ የግንባታ ሥራዎች በመከታተልና የማማከር ሥራዎችን በማከናወን ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረግ እንደሆነም ነው የተገለፀው።

የሁለት ዓመት የኮንትራት ጊዜ በተሰጠው የአጋርነት ሥምምነት መሰረት በኩባንያው እና በተቋሙ የኢንጅነሪንግ ዘርፍ መካከል የልምድ ልውውጦች፣ የሥራ ላይ ሥልጠናዎች እንዲሁም የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር ሥራዎች እንደሚሰሩም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማማከር ሥራዎችን በኢንጅነሪንግ ዘርፍ ሙሉ በሙሉ በራስ አቅም እንዲከናወን የሚያስችል የስትራቴጂክ ግብ ቀርፆ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ በሥምምነቱ ወቅት ተገልጿል።

ዘርፉ ከዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ጋር በአጋርነት የማማከር ሥራዎችን እንዲያከናውን የጀነሬሽን ኮንስትራክሽን ዘርፍ ድርሻው የጎላ መሆኑም ተመላክቷል።

የፕሮጀክቱን የማማከር ሥራዎች ለማከናወን ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ በጀት የተያዘ ሲሆን የፋይናንስ ወጪውም ከዴንማርክ አለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (DANIDA) በተገኘ ብድርና ስጦታ የሚሸፈን ነው።

Scroll to Top