የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የገቢ ምንጩን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሰፈ መምጣቱን በተቋሙ የገበያ እና ቢዝነስ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የሽያጭና ደንበኞች አስተዳደር ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ምኒልክ ጌታሁን እንዳስታወቁት ከዚህ በፊት የተቋሙ የገቢ ምንጭ በኃይል ሽያጭ እና በፋይበር ኦፕቲክስ (OPGW) ኪራይ ላይ ብቻ ተገድቦ የቆየ ነበር።
በአሁኑ ወቅት ተቋሙ የገቢ ምንጩን በማስፋት በተያዘው በጀት ዓመት ከተለያዩ አገልግሎቶች ገቢ ማግኘት መጀመሩንም ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ምኒልክ ገለፃ የአዋጭነት ጥናት በማካሄድ፣ የረጲ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ደረቅ ቆሻሻ ካቃጠለበት አገልግሎት እንዲሁም በዳታ ማይኒንግ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች ኃይል በማቅረብና ሰርቨራቸውን በማከፉፈያ ጣቢያዎች ግቢ ላይ ካስቀመጡበት አገልግሎቶች (Anslery Service) ተቋሙ ተጨማሪ ገቢ እያገኘ ነው።
በዚህም በ2016 በጀት ዓመት ከተጀመሩ አዳዲስ የገቢ ምንጮች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ756 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ነው ሥራ አስኪያጁ የገለፁት።
ከዚህ ውስጥ 555 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብሩ (10 ነጥብ 1 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር) በዳታ ማይኒንግ ሥራ ላይ ከተሳተፉ ድርጅቶች የኃይል አቅርቦት እና 72 ነጥብ 83 ሚሊዮን ብሩ ደግሞ ድርጅቶቹ ሰርቨራቸውን በማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ካስቀመጡበት የአገልግሎት ክፍያ የተገኘ ነው።
በተጨማሪም 6 ነጥብ 11 ሚሊዮን ብሩ ከአዋጭነት ጥናት እንዲሁም 121 ነጥብ 78 ሚሊዮን ብሩ ረጲ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ደረቅ ቆሻሻ ካቃጠለበት የአገልግሎት ክፍያ የተገኘ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ አብራርተዋል።
ተቋሙ የገቢ ምንጩን እያሰፋ በመሄዱ ገቢው ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ የመጣ ሲሆን ለአብነትም በ2012 በጀት ዓመት ከነበረው የ9 ቢሊዮን ብር ገቢ በ2015 በጀት ዓመት ገቢው ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል።
በተያዘው የ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራትም ከ20 ነጥብ 28 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን አቶ ምኒልክ ጠቁመዋል።
አዳዲስ የገቢ ምንጮች ለተቋሙ የገቢ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከቱ መሆኑን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ በቀጣይም የተቋሙን ገቢ የሚያሳድጉ የተለያዩ የገቢ ምንጮችን ተግባራዊ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዳታ ማይኒንግ ሥራ ላይ ለመሳተፋ ለተቋሙ የኃይል አቅርቦት ጥያቄ ካቀረቡት ሃያ አምስት ድርጅቶች እስከ አሁን አራቱ ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን ዘጠኝ ድርጅቶች ደግሞ ሰርቨራቸውን በተቋሙ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግቢ ውስጥ በማስቀመጥ ከተቋሙ ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያስረዳል።