የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አመራርና ሠራተኞች በ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ በተቋሙ የስብሰባ አዳራሽ ውይይት አካሂደዋል፡፡
ውይይቱ ተቋሙ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሰው ኃይል ልማት፣ በፋይናንስ፣ በኃይል ማመንጨት፣ በማስተላለፊያ፣ በማመንጫና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታና የጥገና ሥራዎች እንዲሁም በሪፎርም እና በሌሎች ሥራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
የበጀት ዓመቱን የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ያቀረቡት በተቋሙ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ አንዱዓለም ሲዓ እንደገለፁት በዓለም-አቀፍ ደረጃ ብቁ የሆኑ ሠራተኞችን ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
በዚህም በፕሮጀክት ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ ለሚገኙ የሥራ መሪዎች የፕሮጀክት አስተዳደር ሥልጠና እንዲወስዱ በማድረግ ዓለም-አቀፍ የፕሮጀክት ሥራ አመራር ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ15 ሺህ ጌጋ ዋት ሰዓት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት የዕቅዱን 94 በመቶ ማሳካት መቻሉን የጠቆሙት አቶ አንዱዓለም ይህም ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ14 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመላክተዋል።
የኃይል ማስተላለፍና ማከፋፈል ሥራዎችን አስተማማኝ ለማድረግ የጥገና ሥራዎች በትኩረት ቢሰሩም በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት ዕቅዱን ማሳካት እንዳልተቻለ ጠቅሰዋል።
እንደ ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለሀገር ውስጥ ከቀረበ የኃይል ሽያጭ ከ14 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲሁም ለውጭ ሀገራት ከቀረበው ኃይል ከ78 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል።
አገልግሎት የማይሰጡ የተለያዩ ንብረቶችበማስወገድና ከውዝፍ የንብረት ኢንሹራንስ ካሳ ከ113 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የገለፁት ሥራ አስፈፃሚው ከአላስፈላጊ የመድን ሽፋን ክፍያ፣ ነዳጅ፣ ተሽከርካሪና ማሽነሪ ጥገናዎች ከ112 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳን መቻሉንም ጨምረው ገልፀዋል።
በውይይቱ ላይ የማጠቃለያ ሀሳብ የሰጡት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ እንደገለፁት ለህብረተሰቡ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለማዳረስ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልገሎት ጋር በጋራ እየተሰራ ነው።
የህብረተሰቡን የኃይል ፍላጎት ጥያቄ አስተማማኝ በሆነ መልኩ ለማሟላት የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ግንባታዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ የፕሮጀክት ማማከርና ግንባታ አቅምን በማሳደግ በዓለም-አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ተቋም ለመፍጠር ይሰራል።
በተቋሙ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ እንዲሁም ገፅታውን ለመገንባት በሚሰሩ ሥራዎች ላይ እያንዳንዱ ሠራተኛ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይቱ ላይ ከፕሮጀክት አስተዳደር ሥርዓት፣ በራስ ኃይል የግንባታ ሥራዎችን ከማጠናከር፣ ምቹ የሥራ ከባቢ ከመፍጠር፣ የሠራተኞችን ደህንነት ከማረጋገጥ፣ ከካሳ ክፍያና ስርቆት፣ ከታሪፍ ማሻሻያ፣ ከተሽከርካሪ የመለዋመጫ ዕቃዎች አቅርቦት እንዲሁም ከደመወዝና ጥቅማጥቅም ጋር በተያያዘ ከተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየቶች ቀርበው በዘርፍ ሥራ አስፈፃሚዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።



