የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተሽከርካሪዎቹን እና ማሽነሪዎቹን በራሱ አቅም በመጠገን ባለፉት አስር ወራት 25 ነጥብ 33 ሚሊዮን ብር ወጭ ማዳኑን የተሸከርካሪ ጥገና አስተዳደር ቢሮ ገለፀ፡፡
የቢሮው ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰይድ አህመድ እንደገለፁት ተቋሙ በጋራዡ በተለያዩ ምክንያቶች የሚያጋጥሙ ድንገተኛ የተሽከርካሪ ብልሽቶች፣ የቅድመ መከላከል እና መደበኛ የጥገና ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት ጋራዡ የተቋሙን ተሽከርካሪዎች የቦዲ፣የቀለም ቅብ፣ የ’ኢንጀክሽን ፓምፕ’፣ የሞተርና ሌሎች ከባድ፣ መካከለኛና ቀላል ጥገናዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።
እየተከናወኑ ያሉ የጥገና ሥራዎች ተቋሙን ከተጨማሪ ወጪ እየታደጉት እንደሆነ ያነሱት አቶ ሰይድ ባለፉት 10 ወራትም 1 ሺህ 293 ተሽከርካሪዎችና ማሽነሪዎች ላይ የቀላል፣ መካከለኛና ከባድ የጥገና ሥራዎችን በማከናወን 25 ነጥብ 33 ሚሊዮን ብር ማዳን ተችሏል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ የሥራ ክፍሉ አዲስ ለሚገዙ ተሽከርካሪዎች ዝርዝር የቴክኒክ መስፈርቶችን የማዘጋጀትና በመስፈርቱ መሰረት መቅረባቸውን የማረጋገጥ እንዲሁም በተለያዩ ጋራዦች የሚጠገኑ ተሽከርካሪዎች በአግባቡ መጠገናቸውን የመከታተልና የመፈተሽ ሥራዎችን ያከናውናል።
ቢሮው በኢንሹራንስ የሚሰሩ የተሽከርካሪ ጥገናዎችን እንደሚከታተል እና ባለፉት አስር ወራትም 67 የተቋሙ ተሽከርካሪዎች በኢንሹራንስ የጥገና አገልግሎት ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል።
በጋራዡ ለጥገና ሥራ የሚያስፈልጉ የተለያዩ ዘመናዊ መሳሪያዎችንና የመለዋወጫ ዕቃዎችን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ሰይድ በአሁኑ ወቅትም 70 በመቶ የሚሆነው የመለዋወጫ ዕቃ አቅርቦት ችግር መቀረፉን አንስተዋል።
ምንም እንኳን በጋራዡ ላይ የዘመናዊ መሳሪያዎች እጥረት ቢኖርም ሠራተኞቹ ያላቸውን ልምድና ክህሎት ተጠቅመው ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሆነ ነው አቶ ሰይድ የተናገሩት።
በየዓመቱ ጥገና ከሚደረግላቸው ተሽከርካሪዎች ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው በራስ አቅም እየተከናወነ ሲሆን በቀጣይ የራስ ኃይል አቅምን ለማሳደግ ተቋሙ ለሥራ የሚያስፈልጉ የተለያዩ መሳሪያዎችንና መለዋወጫ ዕቃዎችን በአግባቡ ማሟላት እና ደረጃውን የጠበቀ ጋራዥ መገንባት እንደሚጠበቅበት ሥራ አስኪያጁ አፅንዖት ሰጥተዋል።
የተሽከርካሪ ጥገና ባለሙያዎችን ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ ጋር እንዲተዋወቁ ለማድረግና አቅማቸውን ለማሳደግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሥልጠና እንዲያገኙ መደረጉን አስታውሰው ተጨማሪ ስልጠናዎችን ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም ጠቁመዋል።
አቶ ሰይድ አክለውም ከስልጠና ጎን ለጎን አዲስ ሠራተኞች ከነባሮቹ ጋር እንዲሰሩ በማድረግ የእውቀት ሽግግርና የሥራ ላይ ልምድ ልውውጥ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።