የኢትዮ-ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የወንዶች እግር ኳስ ቡድን ወደ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዳግም እንዲመለስ ላደረጉት ዋና አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ የአንድ ሚሊዮን ብር ሽልማት አበርክቷል።
ክለቡ ወደ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዳግም መመለሱን ተከትሎ ትላንት ምሽት በሒልተን ሆቴል የዕውቅና እና ሽልማት መርሃ-ግብር ተካሂዷል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮ-ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አለማየሁ መንግስቴ እንደገለፁት የስፖርት ክለቡ ከ1953 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራቸውን ወክለው በመወዳደር የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ያደረጉ ዕውቅ ስፖርተኞችን ያፈራ ነው።
እንደ አቶ አለማየሁ ገለፃ ክለቡ ከአራት ዓመታት የከፍተኛ ሊግ ቆይታ በኋላ በ2014 ዓ.ም ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ቢመለስም ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ከፍተኛ ሊግ ወርዷል።
በ2016 ዓ.ም ክለቡ አምስት ጨዋታ እየቀረው ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ድጋሚ መመለሱ እንዳስደሰታቸውም ነው አቶ አለማየሁ የገለፁት።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚና የክለቡ ጠቅላላ ጉባዔ ሰብሳቢ አቶ ሽፈራው ተሊላ እንደገለፁት ክለቡ ዳግም ወደ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በመመለሱ ደስተኛ ነኝ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በኢነርጂ ዘርፍ እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ በስፖርቱ ዘርፍም እየደገሙት መሆኑንም ነው የገለፁት።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚና የክለቡ ጠቅላላ ጉባዔ ምክትል ሰብሳቢ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በበኩላቸው ክለቡ በ2017 ዓ.ም የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዋንጫ ተፎካካሪ ቡድን እንደሚሆን እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል።
የሁለቱ ተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች፣ የስፖርት ማህበሩ አባላት እንዲሁም መላው የስፖርት ቤተሰብ ለክለቡ ስኬታማነት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውንም አቅርበዋል።
በመርሃ-ግብሩ ቡድኑ አምስት ጨዋታ እየቀረው ፕሪሚየር ሊጉን በመቀላቀሉ እንደ ተሳትፏቸው ደረጃ ከ20 ሺህ እስከ 355 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ለተጫዋቾች፣ ለምክትል አሰልጣኞችና ለቡድን መሪዎች እንዲሁም ለድጋፍ ሰጪ አባላት ተበርክቷል።
የስፖርት ክለቡ ውጤት እንዲያመጣ የክትትልና ድጋፍ አስተዋፅኦ ላደረጉት የሁለቱ ተቋማት ዋና ሥራ አስፈፃሚዎችም ሽልማት ተሰጥቷል።
በዕውቅና እና ሽልማት መርሃ-ግብሩ ላይ የሁለቱ ተቋማት ዋና ሥራ አስፈፃሚዎችን ጨምሮ የከፍተኛ ሥራ አመራሮች እንዲሁም
ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።





