የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለወራቤ ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ቦታቸውን ለለቀቁ ተነሺ አርሶ አደሮች የ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የዓይነት ድጋፍ ማድረጉን በተቋሙ የአካባቢና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ባለሙያ አቶ ቤዛ አብርሃም እንደገለፁት የቡታጅራ ወራቤ 132 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ባመቻቸው የመልሶ ማቋቋም ሥራ ለፕሮጀክቱ ግንባታ ሲባል ተገቢው የካሳ ክፍያ ተከፍሏቸው ለተነሱ አርሶ አደሮች ተቋሙ የወተት ላሞችን ገዝቶ ድጋፍ አድርጓል።
ማከፋፈያ ጣቢያው ካረፈበት ቦታ ለተነሱ 11 አርሶ አደሮች ለእያንዳንዳቸው አንድ አንድ የሆልስቲን ዝርያ ያላቸው የወተት ላሞች ከአንድ ወር መኖ ጋር በ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ገዝቶ መስጠቱን የገለፁት ባለሙያው ለቀሪ አምስት አርሶ አደሮችም በቅርቡ ርክክብ ይደረጋል ብለዋል፡፡
የመልሶ ማቋቋም ድጋፉ በአርሶ አደሮቹ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ወደ ፊት ለሌሎች ተሞክሮ የሚሆን ውጤት ተቋሙ ከአርሶ አደሮቹ እንደሚጠብቅ አስገንዝበዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ በዙሪያቸው የሚገኙ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን እንደራሳቸው ንብረት እንዲጠብቁ ባለሙያው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የወራቤ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅና ም/ከንቲባ አቶ ሻፊ ሙዜ በበኩላቸው በልማት የተነሱ አርሶአደሮችን መልሶ ለማቋቋም ተቋሙ ትኩረት በመስጠቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያደረገው ድጋፍ አርሶ አደሮች ራሳቸውን እንዲችሉ ከማድረግ ባሻገር በከተማዋ የሚስተዋለውን ከፍተኛ የወተት እጥረት ለማቃለል እንደሚግዝ ገልፀዋል፡፡
ተቋሙ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት አቶ ሻፊ ከተማ አስተዳደሩ ነዋሪዎችን በማሳተፍ የተገነቡ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን በባለቤትነት እንደሚጠብቅ አረጋግጠዋል፡፡
የስልጤ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ነጃ ሺፋ በበኩላቸው ተቋሙ ለአርሶ አደሮች የገዛቸው የሆልሰቲን ዝርያ ያላቸው ላሞች በቀን በአማካይ ከ20 እስከ 30 ሊትር ወተት ስለሚሰጡ አርሶ አደሮቹ በአጭር ጊዜ ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል፡፡
አርሶ አደሮቹ በርክክብ ሥነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት የተደረገላቸው ድጋፍ ለዕድገታቸው ትልቅ መነሻ በመሆኑ ተቋሙን መቼም እንደማይረሱት እና በተደረገላቸው ድጋፍ ትልቅ ለውጥ በማምጣት የተቋሙን ስም እንደሚያስጠሩም አረጋግጠዋል።
ለማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ ይዞታቸው ሲወሰድ ተቋሙ በቂ ካሳ እንደከፈላቸው እና የከተማ አስተዳደሩም 500 ካሬ ምትክ ቦታ እንደሠጣቸው የጠቀሱት አርሶ አደሮቹ ያሁኑ የመልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍ ተጨማሪ በመሆኑ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከሚገነባቸው የኃይል መሠረተ ልማቶች በተጨማሪ ለአካባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ የማህበራዊ አገልግሎት ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል።



