ለህዳሴ ግድብ ድጋፍ ለማሰባሰብ የተዘጋጀው itsmydam መተግበሪያ ተሻሽሎ ዳግም ሥራ ጀመረ

ለህዳሴ ግድብ ድጋፍ ለማሰባሰብ የተዘጋጀው itsmydam መተግበሪያ ተሻሽሎ ዳግም ሥራ ጀመረ

ላለፉት ሁለት ዓመታት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ ለማሰባሰብ በሥራ ላይ የቆየው itsmydam መተግበሪያ ተሻሽሎ ሥራ ጀመረ፡፡

የተሻሻለው መተግበሪያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በተዘጋጀ መርሀ ግብር ትናንት በይፋ ሥራ ጀምሯል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በመርሀ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት መተግበሪያው ከዚህ በፊት ሥራ ላይ ውሎ ከ250 ሺ ዶላር በላይ ልገሳ ተሰብስቦበታል፡፡

ለአጠቃቀም እንዲመች የተሻሻለው መተግበሪያ ለጋሾች ለሚያደርጉት ልገሳ በኢሜል አድራሻቸው የምስክር ወረቀት ማግኘት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

እንደ አቶ አቤ ገለፃ ለጋሾች የቪዛ እና ማስተር ካርዳቸውን በመጠቀም ባሉበት ሆነው በስልካቸው አማካኝነት ከ5 እስከ 1000 ዶላር መለገስ ይችላሉ፡፡

በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መተግበሪያውን በመጠቀም በመገባደድ ላይ በሚገኘው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ አሻራቸውን እንዲያኖሩ አቶ አቤ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በበኩላቸው 4 በመቶ ሥራ ብቻ የሚቀረውን የግድቡን ግንባታ በቀጣዩ ዓመት ለማጠናቀቅ 40 ቢሊዮን ብር ወይም 850 ሚሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡

ቀሪ ክፍያዎች በአብዛኛው በውጭ ምንዛሪ የሚከፈሉ ከመሆኑ አንፃር በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አስተዋጽኦ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የታለቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አረጋዊ በርሔ በበኩላቸው ጽህፈት ቤቱ ‘በሕብረት ችለናል’ በሚል መሪ ቃል የድጋፍ ማሰባሰብ ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን በመግለጽ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሚችሉት ሁሉ ለግድቡ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይነህ አቅናው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ዳያስፖራው የገንዘብ እና የዓይነት አስተዋጽኦ ቢያበረክትም በመላው ዓለም ከሚገኘው የዳያስፖራ ብዛት እና አቅም አንፃር ሲታይ የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡

ዲጂታል የድጋፍ ማሰባሰቢያ አማራጮች አለመኖር፣ የመረጃ ተደራሽነት እጥረት፣ በሀገር ውስጥ የተቋማት አለመቀናጀት እና ሌሎችንም ከዳያስፖራው ለተገኘው ድጋፍ ማነስ ተግዳሮት እንደነበሩ አቶ በላይነህ አንስተዋል፡፡

በድረ ገጽ እና በመተግበሪያ በሁለት አማራጮች የሚሰራውን Itsmydam የተሰኘው የድጋፍ ማሰባሰቢያ በማበልፀግ ሂደት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪ ኃይል፣ የታላቁ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት እንዲሁም ኤግል ላዮን ሲስተም ቴክኖሎጂ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡

Scroll to Top