በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማከፋፊያ ጣቢያዎች ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ የእሳት አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፊያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ቴክኒካል ድጋፍ ቢሮ ገለጸ፡፡
የቢሮው ሥራ አስኪያጅ አቶ ነፃነት መላኩ እንዳስታወቁት በተቋሙ የማከፋፊያ ጣቢያዎች በተለያዩ ምክንያቶች የእሳት አደጋዎች እየተከሰቱ ይገኛል፡፡
ችግሩን አስቀድሞ ለመከላከል ለአደጋ ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮችን ተከታትሎ በማሰወገድ፣ በየጣቢያው ያሉትን ሠራተኞችን የእሳት አደጋ መከላከያ ስልጠና በመስጠት እና የእሳት አደጋ መከላከያ ስልክ ቁጥሮች በማስቀመጥ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በጣቢያዎቹ እሳት በሚነሳበት ጊዜ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት 16 የእሳት አደጋ መከላከያ መኪኖች መገዛታቸውን ተናግረዋል፡፡
መኪኖቹም የጣቢያዎቹን ተጋላጭነትና ሪጅኖቹ ያላቸውን የማከፋፊያ ጣቢያ ብዛት ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሚሰራጩ እና ሥራውንም በተቋሙ በሰለጠኑ ባለሙያዎች ለማከናወን መታቀዱን አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም በማሰራጫ መስመሮች ብልሽት ምክንያት የሚከሰቱ የእሳት አደጋዎችን ለመከላከል ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በዕቃዎች እርጅና ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ለመቅረፍም በአዲስ የመተካት እና ከፍተኛ የጥገና ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የጣቢያዎችን ዙሪያ አጥር የማጠናከር፣ አካባቢውን የማፅዳትና በመንገድ የማካለል ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት ኃላፊው የተለያዩ መመሪያዎች በማዘጋጀት አሰራሩን ወጥና ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

