የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን በተያዘው በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን በተያዘው በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው

የደጀን-ደብረማርቆስ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ሥራ ከ87 በመቶ በላይ መጠናቀቁን ፕሮጀክቱ አስታወቀ፡፡

በፕሮጀክቱ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳለ ላቀው እንዳስታወቁት የመስመር ዝርጋታው የደጀን ባለ 230/33 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያስችል ነው፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ 48 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍነው የደጀን-ደብረማርቆስ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር 111 የኃይል ማስተላለፊያ ተሸካሚ ምሰሶዎች አሉት፡፡

በአሁኑ ወቅት የ110 የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች የመሠረትና የኮንክሪት ሥራ እንዲሁም የ106 የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች የተከላ ሥራ መጠናቀቁን ሥራ አስኪያጁ ጠቅሰው ቀሪ የመሠረት እና ተከላ ሥራዎች በቅርቡ እንደሚጠናቀቁ ነው የገለፁት፡፡

በ55 የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ የኮንዳክተር ዝርጋታ መከናወኑን የገለፁት አቶ እንዳለ በቀሪ 56 የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ ኮንዳክተር ለመዘርጋት ከወዲሁ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ሥራው በራስ አቅም እየተከናወነ በመሆኑ ከፍተኛ ወጪ ማዳን መቻሉን የጠቀሱት አቶ እንዳለ በዝርጋታ ሥራው ላይ እየተሳተፉ ለሚገኙ ሠራተኞች የዕውቀትና ልምድ ሽግግር እንዲያገኙም ዕድል መፍጠሩን አብራርተዋል፡፡

የደጀን- ደብረማርቆስ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት ከ73 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተመደበለት ሲሆን የፋይናንስ ወጪውም ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሸፈን ነው፡፡

የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክቱን እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ነው አቶ እንዳለ የጠቆሙት፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top