አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት በመኖሩ የፋብሪካው ምርታማነት ጨምሯል

አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት በመኖሩ የፋብሪካው ምርታማነት ጨምሯል

አስተማማኝ ኃይል እየቀረበ በመሆኑ ምርታማነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የሲ ኤንድ ኢ ወንድማማቾች ብረታ ብረት ፋብሪካ አስታወቀ።

የፋብሪካው ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሴፍ ሙሉጌታ እንዳስታወቁት ፋብሪካው በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኝና በአርማታ የብረት ምርት በሀገሪቱ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፍ ነው።

በ2003 ዓ.ም ሥራ የጀመረው ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት ከ650 በላይ ቋሚ፣ ከ45 በላይ ጊዜያዊ እና የተለያየ ሙያዊ ድጋፍ የሚሰጡ የውጭ አገር ሠራተኞችን መያዙን ተናግረዋል።

የብረት ፋብሪካ ከፍተኛ ኃይል የሚጠይቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከአሁን ቀደም በምርት ሥራው ላይ እንቅፋት የሚፈጥር የኃይል መቆራረጥ እንደነበር አስታውሰዋል።

የኃይል መቆራረጡ በፋብሪካው ላይ የሚያደርሰውን ኪሳራ ለማስቀረት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በመነጋገር ከቆቃና ከገላን በሁለት አቅጣጫ ኃይል የሚያገኝ የራሱን ባለ 132 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ገንብቶ ወደ ሥራ ማስገባቱን ገልጸዋል።

ይህም የኃይል መቆራረጡን በማስወገድ የፋብሪካውን ምርታማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዳሳደገው ነው ምክትል ሥራ አስኪያጁ የተናገሩት።

ከተቋሙ ጋር በተደረገ የአገልግሎት ሥምምነት (service level agreement) መሠረት የማከፋፈያ ጣቢያውን የኦፕሬሽን ሥራ እና ሌሎች ሙያዊ ድጋፎች በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለሙያዎች እየተከናወነ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው እስከ 10 ሜጋ ዋት የሚደርስ ኃይል እየተጠቀመ ሲሆን አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት መኖሩን ታሳቢ በማድረግ 10 ሺ ሄክታር ከከተማ አስተዳደሩ ተቀብሎ የማስፋፊያ ሥራ እያከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ የሚፈጸም ስርቆት የፋብሪካውን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን እንገነዘባለን ያሉት አቶ ዮሴፍ እንደ ድርጅት ችግሩን ለመከላከል ወደ ፋብሪካው የሚመጡ ቁርጥራጭ ብረቶችን የሚረከብበት ጠንካራ የቅበላ መመሪያ እንዳለው ተናግረዋል።

ድርጅቱ የሚመጡ ቁርጥራጭ ብረቶች ከመሰረተ ልማቱ ጋር ግንኙነት የሌላቸውና ከስርቆት የጸዱ መሆኑን እያረጋገጠ ከመቀበል በተጨማሪ አጠራጣሪ ነገሮች በሚስተዋልበት ጊዜ ከጸጥታ አካላት ጋር በመነጋገር ጭምር እንደሚሰራ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሲ ኤንድ ኢ ወንድማማቾች ብረታ ብረት ፍብሪካ ባለ132 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ኃላፊ አቶ ጣሰው ተክሌ በበኩላቸው ጣቢያው ከቆቃና ከገላን በሁለት አቅጣጫ ኃይል የሚያገኝ በመሆኑ ያልተቋረጠ የኃይል አማራጭ ለማግኘት አስችሎታል ብለዋል።

ተቋሙ እስከ 40 ሜጋ ዋት ለማቅረብ ዝግጁ ቢሆንም እስከ አሁን ፋብሪካው እየተጠቀመ ያለው ከ10 ሜጋ ዋት ያልበለጠውን መሆኑን አቶ ጣሰው ተናግረዋል።

ፋብሪካው አሁን ላይ ከሚያከናውነው ማስፋፊያ በተጨማሪ ሌሎች የማስፋፊያ ሥራዎችን ቢሰራም አስተማማኝ ኃይል የማቅረብ አቅም መኖሩን አስረድተዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top