ቅንጅታዊ አሰራርን በመዘርጋት የኃይል መቆራረጡን መቀነስ ተችሏል

ቅንጅታዊ አሰራርን በመዘርጋት የኃይል መቆራረጡን መቀነስ ተችሏል

ቅንጅታዊ አሰራር በመዘርጋት የኃይል መቆራረጥን መቀነስ መቻላቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አዳማ 1 ማከፋፈያ ጣቢያ እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዳማ ሪጅን የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።

የአዳማ 1 ማከፋፈያ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ቦንገር እንደገለጹት ሁለቱ ተቋማት የሚሰጡት አገልግሎት ተያያዥነት ያለው በመሆኑ በማህበረሰቡ የሚቀርቡ የኃይል ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲሁም የኃይል ተደራሽነቱን ለማሳደግ ተቋማዊ አሰራሩን በጠበቀ መልኩ ተናበው እየሰሩ ነው፡፡

በከተማዋ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ላላቸው ፋብሪካዎች አስተማማኝ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ የኃይል መቆራረጥ መንስኤዎችን በትብብር ለመቅረፍ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የከተማዋንናና የኢንዱስትሪዎችን ቀጣይ የኃይል ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ በቅርቡ አዳማ ሁለት ባለ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ገንብቶ ወደ ሥራ ማስግባቱንም አውስተዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአዳማ ሪጅን የኔትወርክ መሰረተ ልማት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሬሳ ዓለሙ በበኩላቸው ከማከፋፈያ ጣቢያው 80 ሜጋ ዋት አካባቢ ኃይል እንደሚወስዱና ከጣቢያው ጋር የዕለት ተዕለት ግንኙነት እንዳላቸው አብራርተዋል።

በከተማዋ ያለውን የኃይል ተደራሽነትና የአገልግሎት ጥራቱን ለማሳደግ እንዲሁም በአገልግሎቱ በኩል ምንም የኃይል መቆራረጥ እንዳይኖር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አሁን ላይ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ያለ ኤሌክትሪክ ማግኘት የማይታሰብበት ጊዜ ላይ በመደረሱ የሚመጡ የኃይል ጥያቄዎችን ለመመለስ ቅንጅታዊ አሰራሩን ማጠናከር አማራጭ የሌለው  መሆኑን ነው ሥራ አስኪያጁ የተናገሩት።

የኃይል መቆራረጡ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካ እና ደህንነት ላይ ተጽዕኖ እንዳለው በመረዳት ችግሩን በዘላቂነት በመቅረፍ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዲኖር በተከናወኑ ሥራዎች ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top