ተቋሙ የከተማዋን የኃይል ፍላጎት ታሳቢ አድርጎ እንዲሰራ የከተማ አስተዳደሩ ጥሪ አቀረበ

ተቋሙ የከተማዋን የኃይል ፍላጎት ታሳቢ አድርጎ እንዲሰራ የከተማ አስተዳደሩ ጥሪ አቀረበ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቢሾፍቱ ከተማን የወደፊት የኃይል ፍላጎት ታሳቢ አድርጎ የኃይል መሰረተ ልማቶችን እንዲገነባ የከተማ አስተዳደሩ ጠየቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ገዛኸኝ ደጀኔ እንደተናገሩት ከተማው 63 ሺ ሄክታር የሚሸፍን ስፋት ያለው ሲሆን አሁኑ ወቅት በከተማው 2 ሺ 200 አካባቢ ኢንቨስትመንቶች ይገኛሉ።

ከዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪው መሆኑንና በዘንድሮው በጀት ዓመት ከ250 በላይ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን እንዲሁም ነባሮቹ ትልልቅ የማስፋፊያ ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ይህም ለአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ የሥራ ዕድልን እየፈጠረ ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው ለአብነትም ኢንቨስትመንት በመኖሩ ብቻ በዚህ ዓመት 62 ሺ ለሚሆኑ ወጣቶች በቋሚነት የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቅሰዋል።

እንደ ምክትል ከንቲባው ገለፃ ፋብሪካዎቹ የሥራ ዕድል ከመፍጠር በተጨማሪ ከውጭ የሚገባውን ምርት በመተካት፣ የውጭ ምንዛሬን በማዳንና የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር እንዲኖር በማድረግ የጎላ ሚና አላቸው።

የብረታ ብረት ፋብሪካዎችን ጨምሮ አብዛኛዎቹ በከተማዋ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት የሚጠይቁ ቢሆንም ተቋሙ ቀደም ብሎ ባከናወነው ሥራ አሁን ላይ የኃይል አቅርቦት ችግር አለመኖሩን አንስተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ዘመናዊ የግብርና ሥራን ለማስፋፋት፣ አምራች ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ እና ከተማዋን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ አቅዶ እየሰራ ነው ያሉት አቶ ገዛኸኝ በ5 ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ትልቁ የአየር ማረፊያ በከተማዋ ወደ ግንባታ መግባቱን ገልጸዋል።

በዚህም በየዓመቱ ከ110 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ወደ ከተማዋ ይመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅና ይህን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎችና ወደ ከተማዋ እየመጡ ያሉ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎችን አሁን ላይ ባለው የኃይል አቅርቦት ለማስተናገድ የሚቻል አለመሆኑን ከማከፋፈያ ጣቢያዎቹ ኃላፊዎች ጋር በተደረገ ውይይት መረዳታቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በከተማዋ በቀጣይ ዓመታት ሊኖር የሚችለውን የኃይል ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ሥራ ቀድሞ እንዲያከናውን ምክትል ከንቲባው ጠይቀዋል።

ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግና ከተቋሙ ጋር ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top