የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን የሥራ ኃላፊዎች በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
ለውይይቱ የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደተናገሩት የሁለቱ ተቋማት የአብሮነት ጉዞ አንድ ምዕተ ዓመትን የተሻገረ ነው።
ተቋማቱ ወደ ሁለት ከተከፈሉበት ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ የኮሙኒኬሽን የሥራ ክፍሎች የተቋማቱን ገጽታ ከመገንባት እና ከመረጃ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ በርካታ ሥራዎች ማከናወናቸውን ገልጸዋል።
ይሁንና ከቃላት አጠቃቃም እና ተቀናጅቶ ከመስራት አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውን ያነሱት አቶ ሞገስ በቀጣይ የጋራ የግንኙነት ጊዜ በማስቀመጥ የታዩ ችግሮችን መቅረፍ እና በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ተናቦ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዋር አብራር በበኩላቸው ሁለቱ ተቋማት የሚሰሩት ሥራ ተመጋጋቢ በመሆኑ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን በማጠናከር እና ችግሮችን በማረም በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
አላስፈላጊ መሳሳቦችን በማስወገድ የመረጃ ልውውጡን ማዘመን፣ የጋራ የውይይት መድረኮችን መፍጠር እና ችግሮችን በየጊዜው እየለዩ የጋራ መፍትሄ ማስቀመጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
የሁለቱ ተቋማት የኮሙዩኒኬሽን የሥራ ክፍሎች እስከ አሁን የነበሩ ችግሮችን በሚቀርፍ መልኩ አብረው መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ኮሚቴ አዋቅረዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”





