በኃይል ዘርፉ ያሉ ችግሮችን የሚያቃልሉ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እያከናወንኩ ነው – ዩኒቨርስቲው

በኃይል ዘርፉ ያሉ ችግሮችን የሚያቃልሉ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እያከናወንኩ ነው – ዩኒቨርስቲው

በኢትዮጵያ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የአዳማ ሣይንስና ቴክኒዮሎጅ ዩኒቨርስቲ ገለፀ።

በዩኒቨርስቲው የኤሌክትሪካል ምህንድስና እና ኮምፒውቲንግ ኮሌጁ ምክትል ዲን መስፍን መገራ እንደገለጹት አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ዓለም አቀፍ መለኪያ እየሆነ መጥቷል፡፡

ዘመኑ ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል ምንም ዓይነት አገልግሎት መስጠትም ሆነ ማግኘት የማይታሰብበት በመሆኑ ከተሞችና ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት እና ግብርናን በማዘመን የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የፋይናንስን አገልግሎቶችን ለማሳለጥ እና መረጃዎችን ለመለዋወጥ እንዲሁም መሠረታዊ የሕዝብ ፍላጎቶችን ተደራሽ ለማድረግ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያም እንደሀገር ያሉ ሀብቶቿን አሟጣ በመጠቀም ሁሉን አቀፍ ዕድገት ለማስመዝገብ እና የማህበረሰቡን ሕይወት ለማዘመን ታዳሽ ኃይል አቅርቦት ላይ ትኩረት ሰጥታ በርካታ ተግባራትን እያከናወነች እንድምትገኝ አብራርተዋል።

እንደ አቶ መስፍን ገለፃ ባለፉት ዓመታት ኃይል በማመንጨት ከሀገር ውስጥ አልፎ የጎረቤት ሀገራትን በማስተሳሰር በኩል የተሻሉ ውጤቶች ቢመዘገቡም ሁሉንም የሀገሪቱን አካባቢ ተደራሽ ከማድረግ አንፃር ያሉ ውስንነቶችን መፍታት ይገባል፡፡

የአዳማ ሳይንስና ቴክኒዮሎጅ ዩኒቨርስቲ በኃይል ዘርፉ ላይ እንደሚሳተፍ የትምህርት ተቋም ቀደም ሲል በአዳማ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ላይ ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን የማማከር ሥራ ላይ መሳተፉን ጠቁመዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው ከዋናው ግሪድ ራቅ ባሉ የገጠር አካባቢ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ፀሐይን በመጠቀም በሶላር ኃይል በሚያገኙበት አማራጭ ላይ ሲሰራ መቆየቱን አውስተዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው በኃይል ማመንጨትና በስብጥሩ ዙሪያ ያሉ ክፍተቶች በሚሞሉበት ዙሪያ ጥናትና ምርምሮችን እየተሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ዘርፉን ይበልጥ ለማዘመን እና የኃይል አማራጮችን በማስፋት እንዲሁም የኃይል ብክነትን በመቀነስ ከግሪድ ውጭ የኃይል አቅርቦቱን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የሚሰሩ ጥናትና ምርምሮች ተግባራዊ በሚሆኑበት ዙሪያም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

ዩኒቨርስቲው በቀጣይ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በጥናትና ምርምር እንዲሁም በአቅም ግንባታ ሥራዎች ዙሪያ ተባብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top