የኃይል ማመንጫ ቤት የመጀመሪያ ምዕራፍ የስትራክቸራል ኮንክሪት ሙሌት ሥራ ተጠናቋል

የኃይል ማመንጫ ቤት የመጀመሪያ ምዕራፍ የስትራክቸራል ኮንክሪት ሙሌት ሥራ ተጠናቋል

የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ቤት(Power House) የመጀመሪያ ምዕራፍ የስትራክቸራል ኮንክሪት ሙሌት ሥራ መጠናቀቁን የፕሮጀክቱ የሲቪል መሐንዲስ አስታወቁ፡፡

መሐንዲሱ አቶ ይታገሱ አያሌው እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ የኃይል ልማት ዘርፍ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና ከጊቤ III የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ቀጥሎ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው።

የግድቡ የአርማታ ሙሌት ግንባታ ከመከናወኑ በፊት ከ7 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ልል አፈር የማንሳት ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ከ7 ነጥብ 725 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የአርማታ ሙሌት ውስጥ ከ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የአርማታ ጥቅጥቅ ሙሌት መጠናቀቁንም ነው የጠቆሙት፡፡

ግንባታውን ለማፋጠን በ2 ፈረቃ ለ24 ሰዓታት እየተሰራ መሆኑን የገለፁት አቶ ይታገሱ በየወሩ በአማካኝ ከ100 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ የአርማታ ጥቅጥቅ ሙሌት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ግድቡ አሁን የደረሰበት ከባህር ጠለል በላይ ያለው ከፍታ 623 ሜትር ሲሆን ይህም የግድቡ ቁመት አሁን ላይ 136 ሜትር እንዲሆን ማስቻሉን አንስተዋል፡፡

እንደ አቶ ይታገሱ ገለፃ ግድቡ ሲጠናቀቅ ከባህር ጠለል በላይ ያለው ከፍታ 688 ሜትር ሲሆን አጠቃላይ ቁመቱም 201 ሜትር ይደርሳል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ የስትራክቸራል ኮንክሪት ሙሌት ሥራ መጠናቀቁን ተከትሎ የሁለተኛውን ምዕራፍ የኮንክሪት ሙሌት ለመጀመር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።

ግድቡ እያንዳንዳቸው 300 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው 6 ተርባይኖች ያሉት መሆኑን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሮ ሜካኒካል የተከላ ሥራና የሁሉም ተርባይኖች ክፍሎች በምርት ሒደት ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የግድቡ የውሃ ማስተንፈሻ በሮች ግንባታን ለማጠናቀቅ 7 ነጥብ 7 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ የልል አፈርና የጠንካራ አለት የቁፋሮ ሥራ የተከናወነ ሲሆን የስትራክቸራል የአርማታ ሙሌት ሥራውም 45 በመቶ መጠናቀቁን ገልፀዋል።

የግድቡ ግንባታ እየተከናወነ የሚገኘው በምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ አካባቢ በመሆኑ በቁፋሮ ወቅት የሚያጋጥሙ የተለያዩ የአለት አካላት ግድቡን በሚገባ መሸከም እንዲችሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ መከናወኑን አንስተዋል።

በዚህም በፕሮጀክቱ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን የገለፁት አቶ ይታገሱ ይህም ወደ ፊት ሀገሪቱ በምታከናውናቸው መሰል ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንደሚያስችላቸው አስታውቀዋል።

ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚፈጥረው ሰው ሠራሽ ኃይቅ በአካባቢው ያለውን የቱሪዝም መስህብነት ከፍ እንደሚያደርገው ጠቅሰው መንግሥት በ’ገበታ ለሀገር’ መርሐ-ግብር በኩል ዘርፉን ለማነቃቃት የሰጠውን ትኩረት በመደገፍ በፕሮጀክቱ አካባቢ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

Scroll to Top