ባንኩ ለአይሻ አንድ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የ110 ሚሊዮን ዶላር ብድር አፀደቀ

ባንኩ ለአይሻ አንድ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የ110 ሚሊዮን ዶላር ብድር አፀደቀ


የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ በኢትዮጵያ በመንግሥትና የግል አጋርነት ማዕቀፍ (PPP) ለሚገነባው የመጀመሪያው የአይሻ አንድ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የ110 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማፅደቁን አስታወቀ።

የባንኩ የኢነርጂ ፋይናንስ ሶሊዩሽን ፖሊሲና ሬጉሌሽን ክፍል ዳይሬክተር ዋሌ ሾኒባሬ እንዳስታወቁት ለፕሮጀክቱ ግንባታ የሚውለው ብድር መፅደቁ ለኢትዮጵያ የኃይል ዘርፍ ታሪካዊና አዲስ ምዕራፍ ነው።

ፕሮጀክቱ መቀመጫነቱ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሆነውና በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ በተሰማራው አሜአ ፓወር (AMEA Power) ኩባንያ አማካኝነት የሚገነባና ለ25 ዓመታት በባለቤትነት የሚመራ እንደሆነ ነው ባንኩ የጠቀሰው፡፡

ለፕሮጀክቱ ግንባታ የሚውለው የፋይናንስ ብድር 80 ሚሊዮን ዶላር ከባንኩ፣ 20 ሚሊዮን ዶላር ከንፁህ ቴክኖሎጂ ፈንድ እንዲሁም 10 ሚሊዮን ዶላር ከአፍሪካ ዘላቂ የኢነርጂ ፈንድ የተገኘ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡

ባንኩ ከሌሎች የልማት ፋይናንስ ተቋማት ተጨማሪ 381 ሚሊዮን ዶላር የብድር ድጋፍ ለማሰባሰብ ማቀዱን የገለፀ ሲሆን የተመደበው በጀት የአምስት ኪሎ ሜትር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታንና በነባሩ የአይሻ ሁለት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ የማሻሻያ ሥራን እንደሚያካትትም አብራርቷል።

አጠቃላይ 508 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚጠይቅ የተገመተው ይህ ፕሮጀክት በዓመት 1 ሺህ 189 ጊጋ ዋት ሰዓት ንጹሕ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል።

እንደ ባንኩ ገለፃ ፕሮጀክቱ በ25 ዓመታት የአገልግሎት ዘመኑ ወደ 1 ነጥብ 39 ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ የካርቦን ልቀትን ለመከላከል እንዲሁም በግንባታው ወቅት እስከ 1 ሺህ 525 ለሚደርሱ ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያስችላል።

ፕሮጀክቱ በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ በግሉ ዘርፍ የሚመራ ኢንቨስትመንትን በማፋጠን፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፕሮግራም እንዲሁም ሀገሪቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2030 ሁሉን አቀፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የያዘችውን ግብ በቀጥታ ይደግፋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ የወሰነችውን የካርቦን ልቀትን የመቀነስ አስተዋፅዖ እና የረጅም ጊዜ የተጣራ ዜሮ (Net-Zero) ልቀት ራዕይን የሚያግዝ ሲሆን ብድሩ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2030 ለ300 ሚሊዮን አፍሪካውያን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ ከተቀመጠው የሚሽን 300 (Mission 300) ግብ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣጣም መሆኑን ባንኩ በድረ-ገፁ አስታውቋል፡፡

Scroll to Top